የተመድ ዋና ጸሃፊ ስለድንጋይ ከሰል ምን አሉ?
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወደ ዱባይ በድጋሚ በመመለስ ንግግር አድርገዋል
ጉቴሬዝ በኮፕ28 ጉባኤ ሀገራት ልዩነታቸውን አጥብበው አለምን ከተጋረጠባት አደጋ እንዲታደጉ አሳስበዋል
ከ13 ቀናት በፊት የተጀመረው 28ኛው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በዛሬው እለት ይጠናቀቃል።
በጉባኤው መክፈቻ ንግግር አድርገው የነበሩት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በትናንትናው እለት በድጋሚ ወደ ዱባይ ተመልሰው ንግግር አድርገዋል።
ዋና ጸሃፊው የኮፕ28 ጉባኤ ለአሁኑ እና ለቀጣይ ትውልድ የሚበጁ፤ ዘላቂ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማህበራዊ እድገትን የሚያፋጥኑ፤ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችን የሚቀንሱ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በተለያዩ መድረኮች ከስምምነት መደረሱን አድንቀዋል።
ሀገራት እና ኩባንያዎች በጋራ ጉዳያቸው በትብብር የሚነጋገሩበትን እድል የፈጠረው የዱባዩ ጉባኤ በርካታ የትብብር ቃልኪዳኖች የተፈረሙበት ነው።
ጉባኤው የድንጋይ ከሰል ጉዳይን አንደኛው የመነጋገሪያ ርዕስ አድርጎ ማቅረቡም ይታወቃል።
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በድንጋይ ከሰል ዙሪያ የሚደረገው ንግግር የሀገራትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ በንግግራቸው አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን የድንጋይ ከሰልን ከጥቅም ውጪ ካላደረግን መቀነስ አንችልም ያሉት ጉቴሬዝ፥ ሽግግሩ በእኩል ፍጥነት እና ጊዜ ሊካሄድ እንደማይችል ግን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሀገራት ልዩነቶችን የሚያጠቡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በዱባይ ታሪካዊ ስምምነት እንዲደርሱም ነው የጠየቁት።