የፀጥታው ምክር ቤት በሃውሲ አማጽያን ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ አራዘመ
ዩኤኢ የውሳኔ ሃሳቡ "የአማጽያኑን ወታደራዊ አቅም የሚቀንስ ነው" ብላለች
ማዕቀቡ የአማጺ ቡድኑን አመራሮች ጨምሮ ሁሉንም የቡድን አባላት የሚመለከት ነው ተብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሃውሲ አማጽያን ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ አራዘመ፡፡
ምክር ቤቱ የየመን አማጽያን ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ ያራዘመው በምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (ዩኤኢ) ጥያቄ መሰረት ነው፡፡
በቅርቡ በአማጽያኑ ጥያቄ የተሰነዘረባት ዩኤኢ ምክር ቤቱ አማጽያኑ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብን እንዲጥል ጠይቃለች፡፡ በጥያቄውም ላይ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቧል ድምጽ ተሰጥቶበታል፡፡
11 የምክር ቤቱ አባል ሃገራት የውሳኔ ሃሳቡን ሲደግፉት፣ 4 የምክር ቤት አባላት ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል፡፡ አየርላንድ፣ ሜክሲኮ፣ ብራዚል እና ኖርዌይ የዩኤኢን ሃሳብ ከደገፉ ሀገራት መካከል ናቸው፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት የጣለውን የጦር መሳሪያ ማእቀብ እንደ ከዚህ ቀደሙ በተወሰኑ አመራሮች ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን ሁሉም የሃውሲ አማጽያንን የሚመለከት ነው ተብሏል፡፡
በተመድ የዩኤኢ ቋሚ ተወካይ ላና ኑሴይቤህ የውሳኔ ሃሳቡ "የሃውሲዎችን ወታደራዊ አቅም የሚቀንስ እና በየመን እና በአካባቢው ያለውን ውጥረት ለማርገብ የሚያግዝ ነው" የምክር ቤቱን እርምጃ አድንቀዋል፡፡
በኢራን እንደሚታገዙ ሚነገርላቸው የሃውሲ አማጽያን ባሳለፍነው ጥር ወር በዩኤኢ እና ሳውዲ ዓረቢያ የተለያዩ ጥቃቶች በመሰንዘር በሰው ህይወትና መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወሳል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ አሜሪካ አማጽያኑን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ እያጤንኩኝ ነው ስትል፤ የዓረብ ሊግን ጨምሮ በርካታ ሀገራት አማጽያኑ በዓለም አቀፍ መድረክ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ሲወተውቱ መቆየታቸውም እንዲሁ የሚታወቅ ነው፡፡
አሜሪካ ከአሁን ቀደምም በፕሬዝዳንት ትራምፕ የአስተዳደር ዘመን አመጽያኑን በሽብርተኝነት ፈርጃ ነበር፡፡ ሆኖም አዲሱ የባይደን አስተዳደር ውሳኔውን ቀልብሶ ፍረጃውን አንስቷል፡፡
የሃውሲ አማጽያን ባለፈው ወር ንጹሃን ዜጎችንና መገለወገያዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃትን በአቡ ዳቢ መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡
በጥቃቱ ሁለት ህንዳውያን እና አንድ ፓኪስታናዊ በድምሩ ሶስት ንጹሃን ተገድለዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን በጽኑ እንዲያወግዝና እርምጃ እንዲወስድ ጠይቃ ነበረ፡፡