ኢትዮጵያ የተመድ ሰራተኞች ላይ ባሳለፈችው ውሳኔ ዙሪያ ለማንኛውም አካል ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ የለባትም- አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ
የኢትዮጵያ ውሳኔ ከመንግስታቱ ድርጅት ህግ የተፃረረ ነው- አንቶኒዮ ጉቴሬስ
የተመድ ፀጥታው ም/ቤት ኢትዮጵያ 7 የተመድ ሰራተኞች ከሀገር እንዲወጡ ባሳለፈችው ውሳኔ ዙሪያ ተወያይቷል
የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ትናንት ምሽት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በመንግስታቱ ድርጅት 7 ሰራተኞች ከሃገር እንዲወጡ ባሳለፈው ውሳኔ ዙሪያ ተወያይቷል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ እንቶኒዮ ጉተሬዝ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር “የኢትዮጵያ ውሳኔ ከመንግስታቱ ድርጅት ህግ የተፃረረ ነው፣ ሰራተኞቹን የማባረር መብት የላትም” ብለዋል።
- የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአፋጣኝ ቆሞ ወደ ውይይት መገባት አለበት- የፀጥታው ም/ ቤት
- ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በትግራይ የሚያደርጉትን ድጋፍ በፍጥነት ሊያሳድጉ ይገባል- የፀጥታው ም/ቤት
የአሜሪካ ተወካይ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ መንግስት 7 የተመድ ሰራኞችን ከሀገር እንዲወጡ ላደረገበት ምክንያት ምንም አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ አይችልም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔውን ሊቀለብስ ይገባል” ብለዋል።
ቻይና እና ሩሲያ በበኩላቸው የተናጠል የማዕቀብ እርምጃዎችን ተቃውመው፣ የኢትዮጵያን መንግስት መደገፍ ይገባል ያሉ ሲሆን፣ ከተመድ ሰራተኞች ጋር ላለው ችግርም መፍትሄው ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ብቻ ነው ብለዋል።
በውይይቱ ላይ ተገኝተው የኢትዮጵያን አቋም ያንፀባረቁት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፤ “ሀገራት የተለያዩ የተመድ ሰራተኞችን እና ዲፕሎማቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሀገራቸው ማስወጣታቸውን እናውቃለን፤ ሆኖም ግን ተመድ በእነሱ ላይ ስብሰባ አድርጎ ያውቅ ይሆን” ሲሉም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃውን ስለ መውሰዱ ለማንኛውም አካል ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ እንደሌለበትም አስታውቀዋል።
የተመድ ሰራተኞች የገለልተኝነት መርሆችን በጣሰ መልኩ ለህወሓት የሚወግኑ መሆናቸውን በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ አክለው ገልጸዋል።
ሰራተኞቹ ያልሞቱ ሰዎችን በረሃብ ሞተዋል በሚል የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨት፤ የመገናኛ መሣሪያዎችን ለህወሓት ወገን ማድረስ፤ ህወሃት መቀሌ ሲገባ ከቡድኑ ጋር ደስታቸውን መግለጽ፤ ከሳዑዲ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ሶስተኛ ሀገር በማምጣት ለቡድኑ እንዲዋጉ ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ህወሓትን የሚደግፉ ጹሑፎችን ማዘገጀት ላይ ተጠምደው ነበር ብለዋል።
የአምባሳደር ታዬን ማብራሪያ ተከትሎ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴርስ ባደረጉት ንግግር፤ “ከኢትዮጵያ ስለተባረሩ የተመድ ሰራኞች የደረሰኝ አንድም ማስረጃ የለም” ብለዋል።
“እኛ በኢትዮጵያ ላይ ሌላ አጀንዳ የለንም" ያሉት ጉቴሬስ፤ "እኛ ያለን አጀንዳ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
አምባሳደር ታዬ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ በተመድ እና በኢትዮጵያ መካከል ባቻ በንግግር መፈታት እንዳለበት ጠቅሰው፤ በተባረሩ የተመድ ሰራተኞች ላይ አስፈላጊውን ማስረጃ እንደሚያስገቡ አስታውቀዋል።