መንግስት ከዛሬ ጀምሮ የሚተገበር የተናጠል ተኩስ አቁም በትግራይ ክልል ማወጁን አስታወቀ
ሁሉም የፌዴራልና የክልል ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት፣ ከመንግሥት በሚሰጣቸው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት ተኩስ አቁም እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ታዘዋል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተኩስ እንዲቆም ያቀረበውን ጥያቄ በአዎንታ መቀበሉንም አስታውቋል
ወቅቱን የሚመጥን ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል በሚል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥያቄ በአዎንታ መቀበሉን የፌዴራል መንግስት አስታወቀ፡፡
መንግሥት የቀረበለትን ጥያቄ አስመልክቶ የሰጠውን የውሳኔ ሙሉ ሀሳብ የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ከአሁን ቀደምም ተደጋጋሚ እድሎች ተሰጥተውት እንደነበር ያስታወሰ ሲሆን በእድሎቹ ከመጠቀም ይልቅ ለውጡን የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን በማብዛት የመታረሚያ ዕድሎችን ማበላሸቱን ገልጿል፡፡
“ይባስ ብሎ ግጭቶችን እየጠነሰሰ፣ እልቂት እየደገሠ ሀገር ለማፍረስ መሥራት ቀጠለ” ሲል የሚያትተው መግለጫው በኢሕአዴግ እና በመንግሥት መድረኮች ችግሩን በውይይት ለመፍታት የነበረውን ዕድል አጨናገፈው ሲልም ያስቀምጣል በሃገር ሽማግሌዎችና በሌሎችም መንገዶች የተሞከሩ የሽምግልና መንገዶች መክሸፋቸውን በመጠቆም፡፡
ችግሩን በሆደ ሰፊነት ለማየት የተደረገው ሙከራ እንደ ፍርሓት ተወስዶ በጥቅምት ወር በሰሜን ዕዝ ላይ ሀገር ሊያፈርስ የሚችል ጥቃት ተፈጸመ የሚለው መግለጫው መንግስት ቡድኑን ከጥቅም ውጭ በማድረግ ኢትዮጵያን ለመታደግ በማሰብ ሕግ የማስከበር ዘመቻ መክፈቱንም ያትታል፡፡
መግለጫው “ቡድኑ ሀገራዊ አደጋ ከማይደቅንበት ደረጃ ወርዶ፣ የተረፈው ኃይል የተበተነ ርዝራዥ ሆኗል” የሚልም ሲሆን “ፈፋ ለፈፋ እንደ እየዘለለ የሚኖር ሽፍታ ሆኗል”ም ይላል፡፡
ከዘመቻው መጠናቀቅ በኋላ ከመቶ ቢልዮን ብር በላይ ወደፈጀ መልሶ ግንባታ መገባቱንና ከ30 በላይ የእርዳታ ድርጅቶችና 400 የሚጠጉ ሰራተኞቻቸው ክልሉን ገብተው እንዲረዱ መደረጉንም ይገልጻል፡፡
ሆኖም አንዳንድ ዓለም አቀፍ አጋሮች ለርዳታ የተከፈተላቸውን መሥመር ላልተገባ ተግባር ሲጠቀሙበት ታይተዋል ነው የሚለው፡፡
በተለያየ ጊዜ ከክልሉ ተወላጆች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት የተደረገበት ነው ያለውንና ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተከታታይ ያቀረበውን ጥያቄ ከተለያየ አቅጣጫ መመልከቱንም ነው የገለጸው፡፡
በ6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ለሰላም የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ከግምት ውስጥ በማስገባትና የትግራይ ህዝብ ከሰላሙ ሊቋደስ እንደሚገባ በማመን፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከውጭ ኃይሎች ከተሰነዘሩ ትንኮሳዎች መከላከልና ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ ለመሙላት ትኩረት መስጠት የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑንም ያነሳል፡፡
የክልሉ ገበሬ ተረጋግቶ ወደ እርሻ ሥራ መግባት አለመቻሉን የሚያነሳም ሲሆን ሕዝቡ የጦርነት ጋሻ ሆኖ እየተማገደ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡
በዚህ የተነሣ ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ እርሻቸው የተስተጓጎለባቸው፣ አካባቢያቸውን ለቅቀው የተፈናቀሉ ሁሉ የተረጋጋ ኑሮ ለመኖር አለመቻላቸውን ነው የሚጠቁመው፡፡
“በአንድ በኩል እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በረሐ ከተበተነው ኃይል ውስጥ ሁኔታዎች ቢመቻቹለት ወደ ሰላም ሊመጣ የሚችል ኃይል ይኖራል ተብሎ ስለታመነ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጥያቄ መንግስት በአዎንታዊነት ተቀብሎታል”ም ይላል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ዋነኞቹን የጥፋት መሪዎች ለህግ የማቅረብ ስራ እና፤ የተጀመረው የምርመራ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ገበሬው ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲከውን፣ የርዳታ ሥራው ከወታደራዊ እንቅቃሴ ነጻ ሆኖ እንዲሠራጭ፣ ሰላምን የሚመርጡ የሕወሐት ርዝራዥ አካላት ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ፤ ሳያውቁ ርዝራዡን የጥፋት ኃይል የተከተሉ እንደገና ለማሰብና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል፣ ይህ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለቅድመ ሁኔታ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ከዛሬ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ ማወጁንም ይፋ አድርጓል፡፡
ሁሉም የፌዴራልና የክልል ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት፣ ከመንግሥት በሚሰጣቸው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት ይሄን የተኩስ አቁም እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ታዝዘዋል፡፡
ይሄን መልካም ዕድል ለክፉ የሚጠቀሙ ወገኖች ካጋጠሙ ግን አስፈላጊው ሕግን የማስከበር ተግባር እንደ አግባቡ የሚከናወን ይሆናልም ብሏን መንግስት በመግለጫው፡፡