የሱዳን ጦር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን ጦር በማስለቀቅ የብሔራዊ ተሌቪዥን ጣቢያው ያለበትን ህንጻ ተቆጣጥሬያለሁ ብሏል
የሱዳን ጦር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን ጦር በማስለቀቅ የብሔራዊ ተሌቪዥን ጣቢያው ያለበትን ህንጻ ተቆጣጥሬያለሁ ብሏል።
ይህ 11 ወራትን ባስቆጠረው የሱዳን ጦርነት ለሱዳን ጦር ከፍተኛ ድል ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።
የብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው የናይልን ወንዝ ተሻግሮ በምትገኘው እና የሱዳን ጦር ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በርካታ ቦታዎችን ባስለቀቀበት አምዱርማን ከተማ ይገኛል።
የተባበሩት መንግስት ድርድት(ተመድ) የሱዳን ተፈላሚ ኃይሎች በረመዳን ፆም ወቅት ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ ቢያቀርብም ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
የተኩስ አቁም ጥሪው በፈጥኖ ደራሽ ጦር በኩል ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም በቅርቡ በኦምዱርማን ከተማ የተወሰኑ ቦታዎችን ማስለቀቅ የቻለው የሱዳን ጦር ግን የተኩስ አቁም ጥሪውን አልተቀበለውም።
ሱዳን ጦር የቴሌቪዥን ጣቢያውን መቆጣጠሩ ወንዙን ተሻግሮ በከተማዋ ሰሜናዊ ክፍል ያሉ ይዞታዎችን ለማስፋት ይረዳዋል ተብሏል።
የሱዳን ጦር ጣቢያውን መቆጣጠር የቻለው የእግረኛ ጦር የበላይነት ያላቸውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር፣ በከባድ መሳሪያ ድብደባ እና በአየር ኃይል ጥቃት በመክፈት ነው ሲሉ እማኞች ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ሮይተርስ ይህን ማረጋገጥ እንደማይችል ገልጿል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ጣቢያውን የያዙት በሚያዝያ 2ዐ23 ጦርነቱ እንደተጀመረ ሲሆን ከእዚያ ጊዜ ጀምሮ ለወታራዊ ዘመቻ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።
ብሔራዊ የቴሌቪዥን እና ሬድዮ ጣቢያው ከሱዳን ጦር ጋር የወገኑ ባስልጣናት ከሚኖሩበት በቀይ ባህር ዳርቻ ከምትገኘው ፖርት ሱዳን ስርጭታቸውን ሲያስተላልፉ ቆይተዋል።
በሱዳን ጦር በተለቀቀ ቪዲዮ የሱዳን ጦር አባላት ከጣቢያው በአንድ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሆነው ደስታቸውን ሲገልጹ ይታያሉ።
የሱዳን ጦር ደጋፊዎችም "የሀገሪቱ ድምጽ" ነጻ ወጣ በማለት በማህበራዊ ሚዲያ ደስታቸውን ገልጸዋል።