“የተመድ የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ ሳያርፉ የተመለሱት በስፍራው ካሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው ነው”- መንግስት
የበረራ ፈቃድን አግኝቼ ነበር ያለው ተመድ ድብደባውን በተመለከተ የተሰጠው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እንደሌለ ማስታወቁ የሚታወስ ነው
አውሮፕላኖቹ የተመለሱት በየአየር ጥቃቱ ሳቢያ እንደሆነ በማስመሰል የወጡ ዘገባዎች የተሳሳቱ ናቸውም ብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ ሳያርፉ የተመለሱት በስፍራው ካሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው እንደሆነ መንግስት አስታወቀ፡፡
የእርዳታ አውሮፕላኖቹ የአየር ድብደባውን ተከትሎ ነው የተመለሱት የሚሉ ዘገባዎችን በማስተባበል መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ገጹ በኩል መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው መቀሌ የሚገኘው የወታደራዊ ቡድኑ የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ማእከል በተደበደበበት በትናንትናው ዕለት ከፌደራል መንግስት ፈቃድ አግኝተው ወደዚያው ያቀኑ ሁለት የተመድ የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ እንዳያርፉ በስፍራው ባሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ መከልከላቸውን አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎ “የእርዳታ አውሮፕላኖቹ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው የሚታወቅ ነው”ም ነው መረጃ ማጣሪያው ያለው።
ይህንንም የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱጃሪክ አውሮፕላኖቹ ከፌደራል መንግስት ፈቃድ የተሰጣቸው እንደሆኑና ወደ አዲስ አበባ የተመለሱትም በኤርፖርቱ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው ብቻ መሆኑን ማስታወቃቸውንም አስታውሷል።
ሆኖም “በስፍራው አሉ” የተባሉት እና “ፍቃድ ከለከሉ” የተባሉት የበረራ ተቆጣጣሪዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጀው ህወሓት አባላት ስለመሆናቸው የተገለጸ ነገር የለም፡፡
“የመቀሌውን የአየር ድብደባ በተመለከተ የተሰጠኝ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ የለም”- ተመድ
“እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን የእርዳታ አውሮፕላኖቹ የተመለሱት በየአየር ጥቃቱ ሳቢያ እንደሆነ በማስመሰል የተሳሳተ ዘገባን አውጥተዋል” ነው ያለው መረጃ ማጣሪያው።
የአየር ጥቃቶቹ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተወሰዱና “የሽብር ቡድኑ” ለእኩይ አላማ የሚጠቀምባቸውን የመገናኛና የወታደራዊ ማሰልጠኛዎችን ብቻ ኢላማ ያደረጉ እንደሆኑም ነው ያስታወቀው።
“የሽብር ቡድኑ” ይህንን መሰል የተሳሳቱ መረጃዎችን በማውጣት ህብረተሰቡን በሃሰተኛ ምስሎች ለማወናበድ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ተገንዝቦ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስቧል፡፡
ሁኔታውን በማስመልከት ዛሬ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎች አስተባባሪው ማርቲን ግሪፊትስ መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡
ለበረራ የሚሆኑ አስፈላጊ ፈቃዶችን አግኝተው እንደነበር ያስታወሱት ግሪፊትስ ተቋማቸው ድብደባውን በተመለከተ የተሰጠውም ሆነ የደረሰው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እንደሌለ ነው በመግለጫቸው ያስቀመጡት፡፡
የአየር ድብደባው እና የሰብአዊ እርዳታ ጫኝ አውሮፕላን እንቅስቃሴ አይገናኝም በሚል ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) “ሰዓቱም፣ መዳረሻዎቹም የተለያዩ ናቸው” ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።