በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት ወደ ከተማ የሚገቡትን የስደተኞች ቁጥር “እጅጉን እንዲያሽቅብ” አድርጎታል- የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ
ከትግራይ ወደ ዳባት “አለምዋጭ የስደተኞች ጣቢያ” የተዛወሩ ስደተኞች ቁጥር ከ11 ሺህ በላይ መድረሱም ተመድ አስታውቋል
በአዲስ አበባ 30 ሺህ ብቻ የነበረ የስደተኞች ቁጥር አሁን ላይ ወደ 80 ሺህ አሻቅቧል ተብለዋል
በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭት ወደ ከተማ የሚገቡየስደተኞችን ቁጥር “በእጅጉ እንዲያሻቅብ” ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤን ኤች ሲአር) አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ ማማዱ ዲያን (ዶ/ር) ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በትግራይ የሚገኙት የሽመልባ፣ ሕጻጽ፣ ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ለረዥም ጊዜያት የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ሆነው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በፈረንጆቹ ህዳር 2020 በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭትን ተከትሎ የሽመልባ እና ሕጻጽ መጠሊያ ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ ከመውደማውም ባለፈ በርካታ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎቹን ለቀው ወደ ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ እንዲሸሹ መገደዳቸውን ተወካዩ ገልጸዋል።
ተወካዩ ማማዱ (ዶ/ር)፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኖች ወደ አዲስ አበባና ሌሎች አካባዎች ለመሰደድ መገደዳቸውንም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
በተፈጠረው የጸጥታ ቀውስ ምክንያት በቤንሻንጉል ጉሙዝ፤ የወደመው የጉሬ ሾምቦላ መጠለያ ጣቢያን ጨምሮ ከሌሎች መጠለያ ጣቢያዎች ሸሽተው የመጡ በርካታ ስደተኞች በአዲስ አበባ ይገኛሉም ብለዋል።
ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ 30 ሺህ የነበረው የስደተኞች ቁጥር አሁን ላይ 80 ሺህ መድረሱንም የድርጅቱ ተወካይ ገልጸዋል።በግጭቱ ምክንያት ከየመጠለያ ጣቢያዎቹ ከሸሹት ስደተኞች መካከል በርካቶቹ ኤርትራውያን መሆናቸውም ነው የተገለጸው።
ድርጅቱ፤ የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ ስደተኞችን በተቻለ መጠን ለማገዝ የተለያዩ ጥቶች እያደረገ መሆኑን የገለጹት ማማዱ (ዶ/ር)፤ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር በቂ እንዳለሆነ እንደሚገነዘቡ ተናግረዋል። በመሆኑም ዓለም አቀፍ ለጋሾች አብሮነታቸው ሊያሳዩና የጋራ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ``እንፈልጋለን`` ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
አል-ዐይን አማርኛ፤ ለማማዱ (ዶ/ር) በትግራይ እና በአፋር ክልሎች ስለሚገኙትና በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ ስለሚነገረው የኤርትራ ስደተኞች ጥያቄ አቅርቦላቸዋል።
ተወካዩ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ስደተኞች በግጭቱ ምክንያት ለሞትና እንግልት መዳረጋቸውን ገልጸው፤ እሳቸው የሚመሩት የስደተኞች ኤጀንሲ፤ የተሻለ አገልገሎት ለመስጠት ከመንግስትና ከክልል ባለስልጣናት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለማማዱ (ዶ/ር)፤ ተቋማቸው በትግራይ ከወደሙት የሽመልባ እና ሕጻጽ መጠለያ ጣቢያዎች የተሰደዱትን እንደደገፈ ሁሉ፤ በግጭት ወቅት ከአፋር በራህሌ መጠለያ ጣቢያ የተሰደዱና አሁን ላይ ወደ አፍዴራ እና አብዓላ ተሰደው በሰርዶ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ስደተኞችን ለማገዝም ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አለምዋጭ የስደተኞች ጣቢያ
ከትግራይ ክልል ማይ ዓይኒ መጠለያ ጣቢያ የተዛወሩ ከ11 ሺህ በላይ ስደተኞች በአማራ ክልል ዳባት የአለምዋጭ የስደተኞች ጣቢያ እንደሚገኙ የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በትግራይ የሚገኙ ስደተኞች፤ በክልሉ ሁሉም ሰው የሚያጋጥመውን ችግር እየተጋፈጡ መሆኑን የገለጹት ማማዱ ዲያን (ዶ/ር)፤ ስደተኞችን ወደ ተሻለ ስፍራ ማምጣቱ የተሻለውና አስፈላጊው መፍትሄ እንደነበር ተናግረዋል። ስደተኞቹ ከትግራይ ወደ አማራ ክልል በማምጣቱና በስደተኞች ጣቢያ በማስፈሩ ሂደት የአማራ ክልል ባለስልጣናት ያሳዩት ትብብር “የሚደነቅ” መሆኑን ገልጸዋል።
ማማዱ (ዶ/ር)፤ ይህን ይበሉ እንጂ ከትግራይ ክልል ወደ አማራ ክልል ዳባት “አለምዋጭ የስደተኞች ጣቢያ” የተዛወሩት ኤርትራውያን ስደተኞች ፤ ዳባት እስኪደርሱ እንግልት እንዳጋጠማቸው፤ ከትግራይ ታጣቂዎች ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው እንዲሁም ወደ አለምዋጭ ስደተኛ ጣቢያ ከገቡ በኋላ በተደራጁ ኃይሎች ሰብዓዊ ጥሰት እንደተፈጸመባቸው አል ዐይን አማርኛ ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የስደተኞቹን ደህንነት፤ የሚያጋጥሙ ክስተቶችንና ችግሮችን ለመፍታት ምን እየተሰራ እንደሆነም አል ዐይን አማርኛ በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ተወካይን ጠይቋል።
እርሳቸውም ስደተኞች በተሻለ ሰፍራና ደህንነቱ በጠበቀ መጠለያ ቢሆኑ መኞታቸው መሆኑን ገልጸው፤ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታትና ስደተኞች ከማህበረሰቡ ጋር ተሳስበው በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከፌዴራልና ከክልል መንግስታት ጋር እየተሰራን መሆኑን ተናግረዋል።
ስደተኞቹ፤ ከትግራይ ክልል በእግራቸው እስከ አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ከመጡ በኋላ እስከ ዳባት አለምዋጭ የስደተኞች ጣቢያ የሚጓጓዙበት የትራንስፖርት ሁኔታ መመቻቸቱ ተገልጿል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎች ማለትም ትግራይ፣ አፋር እና አማራ ለረዥም ጊዜያት ስደተኞችን ሲቀበሉ የቆዩ ክልሎች መሆናቸውን የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተለይም የትግራይ ክልል ከ 20 ዓመታት በላይ የኤርትራውያን ስደተኞች ዋና መግቢያና መጠለያ በመሆን ሲያገለግል መቆየቱ ይታወቃል።