የስደተኞች መታወቂያን ይዘው ተገኝተዋል የተባሉ ታጣቂዎችን ጉዳይ እያጣራ እንደሆነ ተመድ ገለጸ
ኤጀንሲውያልተረጋገጡ የግል መረጃዎችን የስደተኞች ናቸው በሚል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ማጋራቱ እንዲቆምም ነው ያሳሰበው
የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ “በቅርቡወደ ኢትዮጵያ በስደተኞች የተደረገ እንቅስቃሴ” አለመመልከቱንም አስታውቋል
“የስደተኞች መታወቂያን ይዘው ተገኝተዋል” የተባሉ ታጣቂዎችን ጉዳይ እያጣራ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
ኤጀንሲው “በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የነበሩና የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ መታወቂያ የያዙ ታጣቂዎች ተገኙ” የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወሩና በተለያዩ የሚድያ አውታሮች ሲዘገቡ መመልከቱን ስለ ጉዳዩ ለጠየቀው አል ዐይን አማርኛ በላከው የኢ-ሜይል መልዕክት አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ሰሞኑን በሱዳን አቅጣጫ መጥተው “ሽንፋ የተባለ ቦታን ለመያዝ የተንቀሳቀሱ የቅማንትና ህወሃት ታጣቂዎች መደምሰሳቸው”ን የሚያሳውቅ ጽሁፍ በትዊተር ገጻቸው ማጋራታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ‘ህወሓት ሰብዓዊ እርዳታን እየዘረፈ ነው’ መባሉን “ከዓለም አቀፍ ተቋማት ሲሰሙ ብቻ መዘገባቸው ለምን ተብሎ መጠየቅ አለበት” ሲል ከትናንት በስቲያ አርብ ያስታወቀው የፌዴራል መንግስትም እየተገኙ ያሉት መታወቂያን መሰል ማስረጃዎች ስደተኛ መስለው ወደ ሱዳን መጠለያ ጣቢያዎች የገቡት የማይካድራ ጭፍጨፋ ፈጻሚ የሳምሪ ቡድን አባላት ተመልሰው ሳይመጡ እንዳልቀረ አመላካች ነው ሲል መግለጹ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከተሎም የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ /ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር/ የኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ቢሮ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ምላሹን የሰጡት የቢሮው ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪች ታጣቂዎቹ ይዘውት ተገኘ ከተባለው “የተመድ የስደተኛ መታወቂያ”ጋር በተያያዘ የወጣውን መረጃ ኤጀንሲው እያጣራ መሆኑን ለአል-ዐይን በላኩት የኢ-ሜይል መልዕክት ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ፤ ሰሞኑን “በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የነበሩና የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ መታወቂያ የያዙ ታጣቂዎች ተመልሰው በግጭቱ ሲሳተፉ ተገኙ” የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወሩና በተለያዩ የሚድያ አውታሮች ሲዘገቡ ተመልክተናል ብለዋል፡፡
ተቋማቸው ጉዳዩን እያጣራ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
ስደተኞቹን የተመለከቱ አዳዲስ መረጃዎች ሲገኙ፣ ከመጠለያ ጣቢያዎች ሲወጡም ሆነ መታወቂያ ካርዳቸው ሲጠፋ የመረጃ ቋታችን የምናዘምንበት በመደበኛ የአሰራር ስርዓት አለን ብለዋል ስደተኞቹ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ሲወስኑ ስደተኛነታቸውን እንደሚያጡ በመጠቆም፡፡
ኤጀንሲው “በቅርቡወደ ኢትዮጵያ በስደተኞች የተደረገ እንቅስቃሴ” አለመመልከቱንም ገልጸዋል ቃል አቀባዩ፡፡
“በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ሆነን የስደት ተመላሾችን የምናረጋግጥበት ሁኔታም የለም”ም ብለዋል ኔቨን ክሬቨንኮቪች፡፡
ኤጀንሲው “የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሲቪል ባህርይን ጠብቀው እንዲቆዩ እና ይህንን ለማረጋገጥ የሚያስችል ድጋፍ ለሱዳን መንግስት ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት” ደጋግሞ መግለጹንም ተናግረዋል፡፡
የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ በቅርቡ ወደ ሱዳን አቅንተው መጠለያ ጣቢያዎቹን ጎብኝተው ነበር፡፡
ግራንዴ በዚሁ ጉብኝታቸው ይህንኑ መግለጻቸውንም ነው ያስታወቁት፡፡
ክሬቨንኮቪች “በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ” የሚለው “መሠረተ ቢስ” ነውም ብለዋል፡፡
ያልተረጋገጡ የግል መረጃዎችን የስደተኞች ናቸው በሚል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ማጋራቱ እንዲቆምም አሳስበዋል፡፡
ይህ በግለሰቦቹ፣ በቤተሰባቸውና በሱዳን በሚገኙ ስደተኞች ላይ ለበቀል እንደሚያነሳሳም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡