ተመድ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ45 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞችን እየደገፈ መሆኑን ገለጸ
በአዲስ አበባ የሚገኙ ስደተኞች “ጊዜያዊ መታወቂያ አግኝተውና የባንክ አካውንት ከፍተው የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ተመቻችቷል”ም ብሏል ተመድ
በትግራይ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች እርዳታ ለማዳረስ አሁንም ከፍተኛ የ ‘ነዳጅ’ ችግር መኖሩን ተመድ አስታውቋል
በኢትዮጵያ የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች እርዳታ እያገኙ መሆናቸውን የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን /የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ/ ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ የኤጀንሲው ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪች በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራውያን ስደተኞች አጠቃላይ ሁኔታን በተመለከተ ከአል-ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸው በትግራይ ክልል ይገኙ የነበሩት የሽመልባ እና ህጻጽ መጠለያ ጣቢያዎች የዛሬ ዓመት በተቀሰቀሰው ግጭት መውደማቸውን ያነሱት ቃል አቀባዩ በጣቢያዎቹ ተጠልለው የነበሩ ስደተኞች ወደ ማይ ዓይኒ እና አዲ ሃሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከካምፕ ውጭ የሚደረግ የኤርትራውያን ስደተኞች እንቅስቃሴ እንዲቆም ጠየቀች
“አሁን ላይ በማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች 25 ሺህ የኤርትራ ስደተኞች አሉ” ሲሉም ነው ክሬቨንኮቪች የተናገሩት፡፡
‘ግጭቱ’ ስደተኞችን ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት ከባድ አድርጎት እንደቆየ ያነሱት ቃል አቀባዩ፤ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የነበረው ሁኔታ በተወሰነ መልኩ የተረጋጋ በመሆኑ የተመድ ሰራተኞች ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ በመሄድ ያለውን ሁኔታ ለመቃኘት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በኮሚሽኑ እና በዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ትብብር አማካኝነት “ከሶስት ሳምንታት በፊት በመጠለያ ጣቢያዎቹ ለሚገኙት ስደተኞች አስፈላጊ ወርሃዊ ምግብ (ራሽን) ተከፋፍሏል” እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፡፡
ቃል አቀባዩ አክለውም ከ8 ሺ በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች ምግብ ነክ ያልሆኑ እንደ የወጥ ቤት ቁሳቁሶች፣ ባልዲ እና አጎበርን የመሳሰሉ ድጋፎች ተደርገዋል ብለዋል፡፡
“ስደተኞቹ የውሃ አቅርቦት እንዲኖራቸው ተደርጓል፤ አሁን ያለው ትልቁ ችግር የጤና አገልግሎት እና እርዳታዎች ለማድረስ የሚያስችለን ‘ነዳጅ’ ማግኘት ላይ ነው”ም ነው ክሬቨንኮቪች ያሉት፡፡
ተጨማሪ 7 ሺ 600 የሚሆኑና ቀደም ሲል በመጠለያ ጣቢያዎቹ የነበሩ ስደተኞችን ለማስተናገድና ለመርዳት በሚቻልበት ዙሪያ “ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር” እየሰራን እንገኛለንም ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ክሬቨንኮቪች በግጭቱ ምክንያት ከመጠለያ ጣቢያዎች ለቀው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ኤርትራውያን ስደተኞች መኖራቸውንም በቆይታው አንስተዋል፡፡
“ወደ አዲስ አበባ የመጡ 20 ሺ ኤርትራውያን ስደተኞች ጊዜያዊ መታወቂያ አግኝተው፤ የባንክ አካውንት ከፍተው የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ለማመቻቸት በመስራት ላይ እንገኛለን”ም ብለዋል፡፡
ኤጀንሲው ከአሁን ቀደም ለአል ዐይን አማርኛ በሰጠው መግለጫ ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኙ የነበሩ ስደተኞችን፤ ‘አለምዋጭ’ ወደተባለና አማራ ክልል ዳባት አካባቢ ወደሚገኝ መጠለያ ጣቢያ የማዛወር እቅድ እንዳለው ገልጾ ነበረ፡፡
ይህን ተከትሎ “እቅዱ የት ደረሰ?” የተባሉት ቃል አቀባዩ ለአዲሱ መጠለያ ጣቢያ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች የማደራጀት ተግባራት በመከናወን ላይ ነው ብለዋል፡፡
ክሬቨንኮቪች፤ እስካሁን 330 ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ‘አለምዋጭ’ መጠለያ ጣቢያ መዛወራቸውን በማስታወቅም “አስፈላጊው እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከጎረቤት ሀገራት የመጡ አንድ ሚሊዮን ገደማ ስደተኞችን እያስተናገደች እንደምትገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን /UNHCR/ ከኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ጋር በመተባበር በስደተኞች ጉዳይ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲሰራ እንደቆየ ይታወቃል፡፡