ተመድ በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 93 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው አለ
ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ያቋረጡት በድርቅ እና ግጭት ምክንያት ነው ብሏል ተመድ
ተመድ በሪፖርቱ 2 ነጥብ 53 ሚሊዮን ህጻናት በግጭት ምክንያት ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ገልጿል
በኢትዮጵያ ከ2 ነጥብ 93 ሚሊየን በላይ ህጻናት በተፈጠረው ግጭትና ድርቅ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ዪኤን ኦቻ) አርብ ዕለት አስታውቋል።
ጽ/ቤቱ ባወጣው ሪፖርት 2 ነጥብ 53 ሚሊዮን ህጻናት በግጭት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ሲሆን 401ሺ ህጻናት ደግሞ በድርቅ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል ብሏል።
ጽ/ቤቱ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል 85 በመቶ ያህሉ ትምህርት ቤቶች እና አፋር እና አማራ ክልሎች የሚገኙ 4ሺ400 ትምህርት ቤቶች ወንበር እና ጠረንጴዛ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።
ሪፖርቱ በመቀጠል ከአንድ ሚሊዮን በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ህጻናትን የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሮች በትምህርት ቤቶች በመዘጋቱ ተጎድተዋል ብሏል።
ጽ/ቤቱ በሪፖርቱ በፈረንጆቹ 2023 በድርቅ መሰፋፋት ምክንያት ሰብአዊ ፍላጎቶች ሊጨምሩ እንደሚችሉ ጠቅሷል።
የዩኤንቻኤ ዘገባ በተጨማሪም በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ሰዎች፣ በሰሜን ኢትዮጵያ 13 ሚሊዮን ዜጎችን ጨምሮ ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውና የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተለይቷል።
ጽ/ቤቱ እንደገለጸው በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰተው ድርቅ እና ሁከትና ብጥብጥ በተጨማሪ በደቡብ ኦሮሚያ ክልል እና በሶማሌ ክልል በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ ከዚህ ቀደም የነበሪ ሰብአዊ ፍላጎቶችን አባብሰዋል።
ይህም በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የእርዳታ አቅርቦት እንዳይደርስ እንቅፋት መፍጠሩን ተመድ ገልጿል።