አሜሪካ ለዩክሬንና ጎረቤቶቿ የ3 ነጥብ 75 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ይፋ አደረገች
ድጋፉ ለኬቭ ሚሳኤሎችንና ዘመናዊ የጦር ተሽከርካሪዎችን ለማቅረብ የሚውል ነው
በሞስኮ የሚፈጸሙ የሚሳይል እና ድሮን ጥቃቶችን የሚመክቱ መቃወሚያዎችም ለዩክሬን ይላካሉ
አሜሪካ ለዩክሬንና በጦርነቱ ምክንያት ተጽዕኖ ለደረሰባቸው ጎረቤቶቿ የ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ወራደራዊ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኗን አስታወቀች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እንደተናገሩት፥ ለኬቭ የሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ የ2 ነጥ8 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ነው።
ከምድር ወደ ሰማይ የሚወነጨፉ ሚሳኤሎች፣ ሮኬቶች፣ የአየር መቃወሚያዎች እና ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን እንደሚሰጡም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
ከፈረንጆቹ 1980 ጀምሮ አሜሪካ በስፋት የምትጠቀምባቸው 50 “ብራድሊ” የተሰኙ የውጊያ ተሽከርካሪዎችም ወደ ኬቭ እንዲላኩ ታዟል።
አሜሪካ የኮንግረንሱን ይሁንታ ሳትጠብቅ በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ብቻ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎች ከክምችቷ ለኬቭ እንዲሰጡ ስትወስን ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም ግዙፉ ነው ተብሏል።
አሜሪካ እና ጀርመን ከዚህ ቀደምም የሩስያን የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃቶች የሚመክት “ፓትሪዮት” የተሰኘ ጸረ ሚሳኤል እንልካለን ማለታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
የዋይትሀውስ ፕረስ ሴክሬተሪ ካሪን ጄን ፔር እንዳስታወቁት፥ ኬቭ የሩስያን የአየር ጥቃቶችን የምትቃወምባቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ከአሜሪካ ታገኛለች።
ይህም የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የሀገራቸውን የሃይል መሰረተ ልማት ያፈራረሱ የሞስኮ ጥቃቶችን የሚያመክኑ የሚሳኤል መቃወሚያዎች ላኩልን ውትወታ ምላሽ ተደርጎ ተወስዷል።
ድጋፉ ዩክሬን በዶንባስ ግዛት ዳግም እንደሚያገረሽ የሚጠበቀውን ጦርነት በበላይነት ለመመከት የሚያስችላት ነው ብለዋል የዋይትሀውስ የብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ።
የዩክሬን ወታደሮች ከአሜሪካ የሚላኩ የጦር መሳሪያዎችን አጠቃቀም በተመለከተ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ስልጠና ይሰጣቸዋል ነው የተባለው።
ዩክሬን ከጦር መሳሪያ ድጋፉ ባሻገር ጦሯን ማዘመኛ የ225 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይደረግላታል።