የሕወሓት አመራሮች የሚገኙበትን ለጠቆመ ዳጎስ ያለ ገንዘብ በሽልማት መልክ ተዘጋጀ
ለመከላከያ በአካል ወይም በስልክ ቁጥር 011 1 248573 ማሳወቅ ይቻላል ተብሏል
አመራሮቹ የሚገኙበትን ለጠቆመ 10 ሚልዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጥ የመከላከያ ሠራዊት አስታወቀ
የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል አስራት ዴኔሮ ዛሬ ረፋድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “የጁንታው” አመራሮችን በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሽልማቱ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በዚህም የመከላከያ ሠራዊት “የሕወሓት ጁንታ” አመራሮች ያሉበትን ቦታ ለጠቆመ የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
የሕወሓት አመራሮች የሚገኙበትን የሚያውቅ ማንኛውም ግለሰብ በአካባቢው ለሚያገኘው የመከላከያ ሠራዊት አባል በአካል በመቅረብ ማሳወቅ አልያም በመከላከያ ሠራዊት የስልክ ቁጥር በ011 1 248573 መጠቆም እንደሚቻልም ተገልጿል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በሕወሓት ኃይል ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ነበር በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በሕወሓት ኃይል መካከል ውጊያ የተጀመረው፡፡ ውጊያው ከተጀመረ 3 ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መከላከያ ሠራዊት የመቐለ ከተማን መቆጣጠሩን ያስታወቀ ሲሆን በወንጀል የሚፈለጉ አብዛኛው የሕወሓት አመራሮችን ግን መቆጣጠር አልቻለም፡፡
መንግሥት በወንጀል ከሚፈልጋቸው ከፍተኛ አመራሮች መካከል እስካሁን ተያዙ የተባሉት የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም እና የቀድሞው የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) ብቻ ናቸው፡፡