አሜሪካ ወደ እስራኤል ቦምብ መላክ አቆመች
የእስራኤል የራፋህ የምድር ውጊያ እቅድ ንጹሃንን በመጠበቅ ረገድ የአሜሪካን ስጋት የሚመልስ ሆኖ አልተገኘም ተብሏል
የኔታንያሁ አስተዳደር ለፔንታጎን ውሳኔ እስካሁን ምላሽ አልስጠም
አሜሪካ ወደ እስራኤል ቦምብ መላክ ማቋረጧ ተገለጸ።
ባለፈው ሳምንት ወደ ቴል አቪቭ ሊላክ ተጭኖ የነበረ 3 ሺህ 500 ቦምብ እንዳይጓዝ የተደረገው በራፋህ ውጊያ ጥቅም ላይ ውሎ ንጹሃን ይጎዳሉ በሚል ነው ብለዋል አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ከሲቢኤስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
ጭነቱ 1 ሺህ 800 ኤምኬ 84 (907 ኪሎራም የሚመዝኑ) እና 1 ሺህ 700 ኤምኬ82 ቦምቦችን ያካተተ እንደነበር ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለስልጣን ተናግረዋል።
የእስራኤል በራፋህ ልትጀምረው ያሰበችውን የምድር ውጊያ በተመለከተ ዝርዝር እቅዷን እንድታቀርብ ስትጠይቅ የቆየችው ዋሽንግተን፥ የጦርነት እቅዱ ንጹሃንን በመጠበቅ ረገድ ስጋቴን ሙሉ በሙሉ የሚመልስ አይደለም ብላለች።
ከአሜሪካ የሚላኩት ቦምቦችም እንደሌሎች የጋዛ አካባቢዎች ሁሉ ህዝብ ጥቅጥቅ ብሎ በሚኖርባት ራፋህ ጥቅም ላይ ውለው በርካታ ንጹሃንን ይቀጠፋሉ በሚል ቦምቦቹ እንዳይንቀሳቀሱ ማገዷን ነው ባለስልጣኑ ያነሱት።
ወልስትሪት ጆርናል ከቀናት በፊት ይህንኑ ዜና ዘግቦት የአሜሪካ ባለስልጣናት ማረጋገጫ ከመስጠት መቆጠባቸው ይታወሳል።
እስራኤልም እስካሁን ስለፔንታጎን ውሳኔ የሰጠችው ምላሽ የለም።
በትናንትናው እለት የራፋህ መተላለፊያን የተቆጣጠረችው ቴል አቪቭ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን በተጠለሉባት ራፋህ የምትፈጽመውን ድብደባ ቀጥላለች፡፡
ከሰኞ ጀምሮ ፍልስጤማውያን ከራፋህ እንዲወጡና በምስራቃዊ የከተማዋ ክፍል እንዲጠለሉ ማድረግ የጀመረች ሲሆን፥ የሀገሪቱ የጦር ካቢኔም የምድር ውጊያው እንዲጀመው ወስኗል።
የእስራኤል ወታደሮች እና ታንኮች በራፋህ ድንበር አካባቢ በብዛት መታየታቸውም ከአየር ጥቃቱ ባሻገር የምድር ውጊያው መቃረቡን አመላካች ነው ተብሏል።
የባይደን አስተዳደር በራፋህ ጦርነት ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ያደረጋቸው ምክክሮች ጦርነቱን ማስቆም አልቻለም።
ባይደን እና ኔታንያሁ ሃማስን በመደምሰሱ ረገድ ተመሳሳይ አቋም ቢይዙም የሚያሳልፉት ውሳኔ ትልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለው መሆኑ ግንኙነታቸውን ፈታኝ እያደረገው ነው።
ከስድስት ወራት በኋላ በዋይትሃውስ ለመቆየት ከትራምፕ ጋር የሚፎካከሩት ባይደን የጋዛው ጦርነት በፍጥነት እንዲቆም ካላደረጉ ዳግም የመመረጥ እድላቸው አደጋ ላይ ይወድቃል።
ኔታንያሁ ባንጻሩ የጥምር መንግስታቸው እንዳይፈርስ የራፋህ ዘመቻውን ማድረግ ግድ ይላቸዋል ይላሉ ተንታኞች።