የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በትግራይ ክልል ቆይታቸው ምን ቃል ገቡ?
የአፋርና የአማራን ጨምሮ የሁሉም ክልል ርእሳነ መስተዳድሮች በመቀሌ ቆይታ አድርገዋል
ክልሎች ለትግራይ ክልል ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል
በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፈራህ የተመራው የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ልዑካን ዛሬ በመቀሌ ቆይታ አድርጓል።
የክልል ርእሳነ መስተዳድሮቹ በመቀሌ ቆይታው ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ለክልሉ መልሶ ግንባታ ሥራዎች 1 ቢሊዮን 675 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ኢ.ዜ.አ ዘግቧል።
የአማራ እና የአፋር ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የሶስቱንም ክልሎች ህዝብ በጋራ ልማት ለማሻገር እንሠራለን ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ 30 ትራክተር እና የምርጥ ዘር አቅርቦት ለትግራይ ክልል ድጋፍ እንደሚደረግ አንስተው፤ አንድ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ለመገንባትም ቃል ገብተዋል።
የክልሉ ህዝብ ካለው ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን አንስተው በዚህም በአጠቃላይ 1 ቢሊዮን ብር የሚሆን የልማት ተሳትፎ እናደርጋለን ነው ማለታቸውን ነው ዘዘገባው የሚያመላክተው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትግራይ ክልልን መልሶ ማቋቋም ስራ ለማጠናከር አንድ ጤና ጣቢያ እና አንድ ትምህርት ቤት መገንባትን ጨምሮ በመጀመሪያው ዙር እስከ 500 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በጉብኝቱ "አጋርነታችንን ለማሳየት ሁለት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ፤ በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት በጋራ ርብርብ መስራትን የሚጠይቅ በመሆኑ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገናል ነው ያሉት።
የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ሰላማችንን ለማፅናት የሁሉም ትብብር ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ ከቁሳቁስ ባሻገር 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን የክልሉ ህዝብና መንግስት ከትግራይ ህዝብ ጎን መቆሙን ለማረጋገጥ 15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ፤ ክልሉ አዲስ ቢሆንም የትግራይ ህዝብን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል። በቀጣይም 2 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ርስቱ ይርዳው፤ የደቡብ ህዝቦች 1 ሺህ 500 ኩንታል የዘር ግብዓት እና የእርሻ መሳሪያዎችን ጨምሮ 20 ሚሊዮን ብር የዓይነት እንዲሁም 30 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ፤ የክልሉ ህዝብ በትግራይ ክልል የሚኖሩ ወገኖቹን ለማገዝ 20 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፥ በተጨማሪም የ10 ሚሊዮን ብር የአይነት ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ነስራ አብደላ በተመሳሳይ ክልሉ በመጀመሪያ ዙር 10 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በበኩሉ 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባን ኢዜአ በዘገባው አመላክቷል።