ፖለቲካ
አሜሪካና አጋሮቿ 'አደገኛና ጠብአጫሪ' ሲሉ የቻይናን እንቅስቃሴ አወገዙ
ሦስቱ ሀገራት በቀውስ ጊዜ ለመመካከርና ለቀጣናዊ ችግሮች በትብብር ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብተዋል
ሀገራቱ አርብ ዕለት የሦስትዮሽ ጉባኤ አድርገዋል
አሜሪካ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ጠንካራ አቋማቸውን ባሳዩበት መግለጫ፤ በደቡብ ቻይና ባህር ላይ የቤጂንግን "አደገኛ እና ጠብአጫሪ እርምጃዎች" አውግዘዋል።
አጋሮቹ በአሜሪካ ባካሄዱት ጉባኤ፤ በቀውስ ጊዜ ለመመካከርና ለቀጣናዊ ችግሮች፣ ቅስቀሳዎችና የጋራ ጥቅሞችን በሚያሰጉ ጉዳዮች ላይ በትብብር ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
ሦስቱ ሀገራት ዓመታዊ የሦስትዮሽ ወታደራዊ ልምምዶችን ለማድረግ እንዲሁም በሰሜን ኮሪያ ላይ ያላቸውን መረጃ ለመለዋወጥ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።
ሀገራቱ በየዓመቱ የሦስትዮሽ ስብሰባዎችን ለማድረግም ቃል ገብተዋል።
አጋሮቹ የቻይናን መነሳት እና የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር አደጋ ለመከላከል አንድነት ለመፍጠር ፍላጎት አላቸው።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ላይ ያላቸውን አቋምና ድጋፍ የገለጹት ሀገራቱ፤ ሮይተርስ እንደዘገበው ቻይና ላይ የተጠቀሙት ቋንቋ ግን ጠንካራ ነው።
በጋራ መግለጫው ከተጠበቀው በላይ ጎልቶ የወጣው የቻይና ጉዳይ፤ ከቤጂንግ ምላሽ ሊጠብቀው ይችላል ተብሏል።