የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኬቭ የጦር መሳሪያዋ እያለቀ በመሆኑ ከባድ ውሳኔ አሳልፈናል ብለዋል
አሜሪካ ለዩክሬን ክላስተር ቦምብ ለመላክ መወሰኗ ተነገረ።
ፔንታጎን ለኬቭ የ800 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ ባደረገ በስአታት ልዩነት ነው የክላስተር ቦምብ የመላክ ውሳኔ ዜናው የተሰማው።
የፕሬዝዳንት ባይደን የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫኒ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ “ክላስተር ቦምቦች ወዲያውኑ ካልፈነዱ በንጹሃን ላይ ሊያደርሱት የሚችሉትን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት እስካሁን ሳንልክ ቆይተናል” ብለዋል።
“ይሁን እንጂ የጦር መሳሪያ ችግር የገጠማት ዩክሬን ይበልጥ ይዞታዎቿን በሩሲያ እንዳትነጠቅ ስንል ከውሳኔ ላይ ደርሰናል” ሲሉም ነው የተደመጡት።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም የጃክ ሱሊቫኒን ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል።
“እጅግ ከባድ” ያሉት ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጊዜ እንደወሰደባቸውና ኬቭ የገጠማት የተተኳሽ እጥረት ፈጣን ውሳኔ እንዲያሳልፉ እንዳስገደዳቸው አብራርተዋል።
ክላስተር ቦምብ ምንድን ነው?
ክላስተር ቦምብ በርካታ ትንንሽ ቦምቦችን የሚይዝና ከምድር ወደ ሰማይ የሚተኮስ ነው።
ትንንሽ ቦምቦቹ ወደ መሬት በተለያየ አቅጣጫ ከወረዱ በኋላ እንዳረፉ ይፈነዳሉ፤ በቀዝቃዛ እና ለስላሳ መሬት ላይ ከወደቁ ግን ላይፈነዱ ይችላሉ።
በዚህም በተለይ ህጻናት መጫወቻ መስሏቸው ሲያነሷቸው ሊፈነዱ የመቻላቸው ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል።
በርካታ ንጹሃንን አደጋ ላይ የሚጥለው የክላስተር ቦምብ ከ100 በላይ ሀገራት ጥቅም ላይ እንዳይወል መታገዱን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ግን ይህን መሳሪያ በተደጋጋሚ ሲጠቀሙበት ታይቷል።
በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የሚቃወሙትን የጦር መሳሪያ ላለመጠቀም ስምምነት ያልፈረመችው አሜሪካም ወደ ኬቭ ልትልክ ውሳኔ ላይ ደርሳለች።
ዩክሬን ውሳኔውን “ጊዜውን የጠበቀና በሩሲያ ላይ የስነልቦና ተጽዕኖ የሚያሳድር” ብላዋለች።
በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ በበኩላቸው ፥ “በአሜሪካ የተሳሳተ ውሳኔ ዩክሬናውያን ለአመታት በቦምብ ይጋያሉ” ሲሉ የባይደንን ውሳኔ ተቃውመዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም የክላስተር ቦምቦች ጥቅም ላይ መዋልን እንደሚቃወሙ መግለጻቸውን የድርጅታቸው ቃልአቀባይ አስታውቋል።
የአሜሪካ ፖለቲከኞችም በክላስተር ቦምብ የመላክ ውሳኔው በሁለት ጎራ ተከፍለዋል።