አሜሪካ አዲስ የኑክሌር ጦርነት ፖሊሲ ማዘጋጀቷ ተገለጸ
ፕሬዝዳንት ባይደን የቻይናን ኑክሌር እንቅስቃሴ ለመገደብ ያለመ ሚስጢራዊ ፖሊሲ ላይ ፈርመዋል ተብሏል
ቻይና በበኩሏ አሜሪካ የዓለማችን ቁጥር አንድ የኑክሌር ጦርነት ስጋት ነች ብላለች
አሜሪካ አዲስ የኑክሌር ጦርነት ፖሊሲ ማዘጋጀቷ ተገለጸ።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ የቻይናን ግስጋሴ ለመግታት በሚል አዲስ የኑክሌር ጦር ፖሊሲ ማዘጋጀቷ ተገልጿል።
በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ ተዘጋጅቷል የተባለው ይህ ሚስጢራዊ ፖሊሲ ዋና ዓላማው የዓለማችን ቁጥር ሁለት ልዕለ ሀያል ሀገር ቻይናን ለማስቆም ነው ተብሏል።
ይህ የኑክሌር ጦር ፖሊሲ በየ አራት ዓመቱ እንዲከለስ የሚያስገድድ ሲሆን ዋሽንግተን የቤጂንግን ግስጋሴ ለማስቆም ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
"የኑክሌር ጦር መመሪያ" ስያሜ የተሰጠው ይህ አዲስ ፖሊሲ ቻይና የአሜሪካን የበላይነት ለመንጠቅ ዋና ተገዳዳሪ ሀገር ነች በሚል እሳቤ እንዲሁም ይህን ስጋት ለማስቆም በሚል መዘጋጀቱን ኒዮርክ ታየምስ ዘግቧል።
ዘገባው አክሎም ይህ የኑክሌር ጦር ፖሊሲ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስልጣናቸውን በመጪው ሕዳር ወር ላይ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለሚያሸንፈው ተመራጭ ከማስረከባቸው በፊት ለሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አስቀርበው እንደሚያጸድቁት ይጠበቃል ተብሏል።
ቻይና በበኩሏ አሜሪካ የዓለማችን ቁጥር አንድ ኑክሌር ጦርነት ስጋት ነች ስትል ምላሽ ሰጥታለች።
የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ እንዳሉት ቻይና የአሜሪካ አዲሱ የኑክሌር ጦር ፖሊሲ እንዳሳሰባት ተናግረዋል።
አሜሪካ እና ቻይና ላለፉት ዓመታት አንዳቸው በአንዳቸው ላይ የንግድ ማዕቀቦችን ሲጥሉ ቆይተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ደግሞ አለመግባባታቸው ከንግድ ታሪፍ መጣል አልፎ ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ እያመራ ይገኛል።