አሜሪካ በኢራቅ እና ሶሪያ የአይኤስ ዋና መሪን ገደልኩ አለች
አቡ ሃዲጃ የተባለው ግለሰብ በምዕራባዊ ኢራቅ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ነው መገደሉ የተነገረው

የሽብር መሪው በሁለቱ ሀገራት የሚንቀሳቀሰውን ቡድን ከመምራት ባለፈ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ዘመቻዎች ዋና ሃላፊ ነበር
አሜሪካ በኢራቅ እና ሶሪያ የአይኤስ መሪ አብደላህ መኪ ሙስሊህ አል-ሪፋይ (አቡ ሃዲጃን) በምዕራባዊ ኢራቅ በፈጸመችው የአየር ጥቃት መግደሏን አስታወቀች፡፡
ላፉት አመታት በአሜሪካ በጥብቅ ሲፈለጉ ከነበሩ ሽብርተኛ ቡድን መሪዎች መካከል አንዱ የነበረው አቡ ሃዲጃ በኢራቅ እና ሶሪያ የሚንቀሳቀሰውን ቡድን ከመምራት ባለፈ የአይኤስ የአለም አቀፍ ዘመቻዎች አዛዥ እንደነበረ ተነግሯል፡፡
የአሜሪካው ማዕከላዊ ኮማንድ (ሴንትኮም) ከኢራቅ የመረጃ እና የደህንነት ሃይሎች ጋር በመተባበር በአል አንባር ግዛት በተፈጸመ የአየር ጥቃት መሪውን መገደሉን ስለዘመቻው ባሰራጨው መረጃ ላይ ጠቅሷል፡፡
መግለጫው አክሎም ጥቃቱ በተፈጸመበት ግለሰቡ በሚጠቀምበት ተሸከርካሪ ውስጥ በተደረገ ምርመራ ያልፈነዳ የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ የታጠቁ ሁለት አስክሬኖች መገኘታቸውን እና የአቡ ሀዲጃ አስክሬን በዲኤንኤ ምርመራ መረጋገጡን ገልጿል።
የማዕከላዊ ዕዙ አዛዥ ጀነራል ማይክል ኤሪክ በሀዲጃ ላይ የተፈጸመውን ዘመቻ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ አቡ ሀዲጃ በአለም አቀፍ የአይኤስ ማዋቅር ውስጥ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት አባላት አንዱ ነበር ብለዋል።
በተጨማሪም “አሸባሪዎችን መግደል መዋቅራቸውን ማፈራረስ በአሜሪካ እና በአጋሮቻችን እንዲሁም በአለም አቀፍ ሰላም ላይ የሚፈጥሩትን ስጋት እናስወግዳለን” ነው ያሉት፡፡
ከሀሙሱ ጥቃት በኋላ የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሺአ አል ሱዳኒ ሀዲጃን "በኢራቅ እና በአለም ላይ ካሉ እጅግ አደገኛ አሸባሪዎች መካል አንዱ ነበር" ሲሉ ገልፀውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “ኢራቃውያን በጨለማ እና በሽብርተኝነት ኃይሎች ላይ ያስመዘገቡትን አስደናቂ ድል ይቀጥላሉ” ብለዋል፡፡
የአየር ጥቃቱ የሶሪያ ከፍተኛ ዲፕሎማት ወደ ኢራቅ ካደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ጋር የተገናኘ ሲሆን ሁለቱ ሀገራት አይኤስን ለመዋጋት በጋራ ለመስራት ቃል ገብተዋል።
ከሶሪያው መሪ በሽር አላሳድ መውደቅ በኋላ በኢራቅ እና ሶሪያ የሚንቀሳቀሰው የአይኤስ ክንፍ ድጋሚ በማንሰራራት ላይ እንደሚገኝ ሪፖርቶች እየወጡ ነበር፡፡
አሜሪካ እና ኢራቅ በመስከረም 2025 በኢራቅ የሚንቀሳቀሰውን አይኤስ ለማጥፋት የጋራ ወታደራዊ ተልዕኮ ለመምራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡