ሰሜን ኮሪያ፤ አሜሪካ ትንኮሳዋን የማታቆም ከሆነ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ አስጠነቀቀች
ሴኡል እና ዋሽንግተን ከፒዮንጊያንግ ጋር የገቡት ፍጥጫ የቀጠናውን በጦርነት እንዳያምሰው ተሰግቷል
ዋሽንግተን እና ሴኡል በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያው ነው የተባለለት ወታደራዊ ልምመድ ጀምረዋል
ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ ትንኮሳዋን የማታቆም ከሆነ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ አስጠነቀቀች።
ፒዮንጊያንግ ባወጣችው የማስጠንቀቂያ መግለጫ በዋሽንግተን እና በደቡብ ኮሪያ መካከል የሚደረገውን መጠነ ሰፊ የአየር ልምምድ “ግጭት ቀስቃሽ” ነው ብላዋልች።
የሀገራቱ ጥምር ጦር ልምምድ እንቅልፍ እንደነሳት የገለጸችው ፒዮንጊያንግ ሀገራቱ ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ እርምጃ እንደመትወስድም ነው ኖርዝ ኮሪያ ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ አንድ የኮሪያ ባለስልጣንን ዋቢ አድርጎ የዘገበው።
የሰሜን ኮሪያው ባለስልጣን ሀገራቸው "ሉዓላዊነቷን፣ የህዝቦቿን ደህንነት እና የግዛት አንድነቷን ከማንኛውም የውጭ ወታደራዊ ስጋት ለመከላከል አስፈላጊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ ናት" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዋሽንግተን እና ሴኡል በትናንትናው እለት በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያው ነው የተባለለትንና አስከ አርብ ድረስ የሚቀጥል ግዙፍ የአየር ልምምድ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ስውር አውሮፕላኖችን ጨምሮ ከ240 በላይ አውሮፕላኖችን ከሰማይ በላይ በማሰባሰብ በኮሪያ ልሳነ ምድር ልምምዳቸው እያደረጉ ነው፡፡
ይህ የሆነው ፒዮንግያንግ በቅርቡ የኒውክሌር ሙከራ ልታደርግ ነው የሚል ግምት እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ በቅርቡ በአወዛጋቢው የባር ድንበር አከባቢ ማስጠንቀቂያ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ተከትሎ በሁለቱም ኮሪያዎች ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል ሲዘገብ ቆይቷል።
እስካሁን በሁለቱም ኮሪያዎች መካካል ጦርነት መደረጉ የሚያመላክቱ ሪፖርቶች ባይኖሩም በኮሪያ ባረ ሰላጤ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ያለው የባህር ድንበር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ደህንነት ስጋት ምንጭ መሆኑ ይታወቃል።
እናም የሴኡል እና ዋሽንግተን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ሰሜን ኮሪያ ከምታስቀነጨፍቸው የባላስቲክ ሚሳዔል ጋር ተዳምሮ ቀጠናውን ወደለየለት ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዳይወስደው ተሰግቷል።
በሁኔታው የተደናገጠው የጸጥታው ምክር ቤትም ቢሆን በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማእቀቦች ለመጣል በተላያዩ ምክረ ሀሳቦች ዙሪያ ሲመክር ይስተዋላል።