የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት አፈ ጉባኤ የመምረጥ ሂደት ለ11ኛ ጊዜ ከሸፈ
የቀድሞው የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ከውድድር ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል
ሪፐብሊካኑ ማካርቲ እጩ ሆነው ቢቀርቡም የምክር ቤቱ አባላት አለመስማማታቸው ተገልጿል
የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት አፈ ጉባኤ ለመምረጥ ለ11 ጊዜ ከሸፈ።
የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምክር ቤት ምርጫ ከአንድ ወር በፊት ተካሂዶ አዲስ የምክር ቤት አባላት መመረጣቸው ይታወሳል።
እነዚህ አዲስ የምክር ቤት አባላት ከያዝነው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮ ስራ ጀምረዋል።
ይህ ምክር ቤት የመጀመሪያ ስራው የምክር ቤቱን አፈ ጉባኤ መምረጥ ቢሆንም ላለፉት አምስት ቀናት ባደረገው ጉባኤ ከስምምነት ሊደርሱ እንዳልቻሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
በሪፐብሊካኖች የበላይነት የተያዘው ይህ ምክር ቤቱ ባለፉት ቀናት ለ11 ጊዜ ተሰብስቦ አፈ ጉባኤ ለመምረጥ ቢሞክርም አባላቱ በመከፋፈላቸው ምክንያት አዲስ አፈ ጉባኤ ሳይመረጥ ቀርቷል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ለ12ኛ ጊዜ እንደሚሰበሰብ የሚጠበቅ ሲሆን እጩ የሆኑት ማካርቲ አሁንም የመመረጥ እድላቸው አነስተኛ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ለመምረጥ ሲቸገር ከፈረንጆቹ 1850 ዓመት ጀምሮ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
አሜሪካ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት የምክር ቤቱን አፈ ጉባኤ ለመምረጥ ተቸግረው እንደነበር ተገልጿል።
የምክር ቤቱ እጩ አፈ ጉባኤ ሆነው የቀረቡት ማካርቲ በቅርብ ጓደኞቻቸው ሳይቀር እምነት የማይጣልባቸው ናቸው መባላቸውን ተከትሎ ለአፈ ጉባኤነት የሚያበቃ ድጋፍ ከምክር ቤቱ ማግኘት አልቻሉም።
ካሊፎርኒያን ወክለው ለአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት በአባልነት የተመረጡት ማካርቲ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ እንደሆኑ ይነገራል።
እጩ አፈ ጉባኤው የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን የሰጡትን የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ድጋፍ ኦዲት እንዲደረግ ማድረግ፣ በቤተሰባቸው ላይ ምርመራ እንዲደረግ እንደሚያደርጉ ከዚህ በፊት ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በምርመራው ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከስልጣናቸው ሊነሱ እንደሚችሉም እጩ አፈ ጉባኤው ከዚህ በፊት ከብዙሀን መገናኛዎች ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ ጠቅሰውም ነበር።