አሜሪካ ለዩክሬን የ100 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባች
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሊዮድ ኦስቲን በኬቭ ከፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ጋር መክረዋል
ዋሽንግተን ለኬቭ ያደረገችው ወታደራዊ ድጋፍ ከ44 ቢሊየን ዶላር በላይ ደርሷል
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዮድ ኦስቲን በትናንትናው እለት በዩክሬን ያልተጠበቀ ጉብኝት አድርገዋል።
ከፖላንድ በባቡር ወደ ኬቭ የዘለቁት ሚኒስትሩ ሀገራቸው ለዩክሬን የማያቋርጥ ድጋፍ እንደምታደርግ ለፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ አረጋግጠውላቸዋል።
ፔንታጎን 100 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ከክምችቱ ወደ ዩክሬን እንደሚልክም ነው የተናገሩት።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪም “እንተማመንባችኋለን” ያሏቸውን የአሜሪካ ኮንግረንስ እና ህዝብ አመስግነዋል።
ፕሬዝዳንቱ በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ምክንያት አለም ከኬቭ ፊቱን አዙሯል የሚል አስተያየት በቅርቡ መስጠታችው ይታወሳል።
በኬቭ ከሚያዚያ 2022 በኋላ ጉብኝታቸውን ያደረጉት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትርም የዋሽንግተን ድጋፍ ሞስኮ ተሸንፋ ከዩክሬን እስክትወጣ ድረስ ይቀጥላል ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
አሜሪካ እስካሁን ለዩክሬን ያደረገችው ወታደራዊ ድጋፍ ከ44 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱን የሚጠቅሰው ዘገባው፥ ሌሎች አጋሮች 35 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ መሳሪያዎች መላካቸውን አውስቷል።
ይሁን እንጂ ኬቭ የመልሶ ማጥቃቷን የተሳካ ለማድረግ አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ - 16 ጄቶች እና ቃል የተገቡላት መሳሪያዎች በፍጥነት እንዲደርሷት መወትወቷን ቀጥላለች።
ዩክሬን በቀጣዩ ክረምት የመልሶ ማጥቃት እንደምትጀምር ይጠበቃል፤ ለዚህም ዩክሬናውያን ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።