አሜሪካ የውርጃ መድሃኒቶች በችርቻሮ መደብሮች እንዲሸጡ ፈቀደች
ከ10 እስከ 15 ሳምንታት የሆነውን ጽንስ የሚያቋርጠው ማይፍፕሪስተን የተሰኘው መድሃኒት ነው በመደብሮች እንዲሸጥ የተወሰነው
የአሜሪካ ምግብና መድሃኒት አስተዳደር ያሳለፈውን ውሳኔ ግን ሁሉም ግዛቶች ተፈጻሚ አያደርጉትም ተብሏል
አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ማይፍፕሪስተን የተሰኘው የጽንስ ማስወረጃ መድሃኒት በችርቻሮ የመድሃኒት መደብሮች እንዲሸጥ ፈቀደች።
የሀገሪቱ ምግብና መድሃኒት አስተዳደር ያሳለፈው ውሳኔ የባይደን አስተዳደር ጽንስ በማቋረጥ ዙሪያ የገባውን ቃል መፈጸሙን ያሳያል ተብሏል።
ሚሶፕሮስቶል ከተባለው መድሃኒት ጋር በጥምረት የሚወሰደው ማይፍፕሪስተን ከ10 እስከ 15 ሳምንታት የሆነውን ጽንስ በማስወረድ ረገድ ውጤታማ ስለመሆኑ ተነግሯል።
በአሜሪካ ከሚቋረጡ ጽንሶች ከግማሽ በላዩ በመድሃኒት የሚከናወን ሲሆን፥ በቀዶ ህክምና ጽንስ የሚያስወርዱትም ቁጥርም ከፍተኛ ነው።
የአሜሪካ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር አስተዳደር በታህሳስ ወር 2021 ያለ ሃኪሞች የፈቃድ ትዕዛዝ መድሃኒቱን ማንኛውም ሰው በመድሃኒት መደብሮች መግዛት እንዲችል መወሰኑ የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችል ያልተፈለገ ጽንስን ለማቋረጥ የተወሰነው ውሳኔ አሁን ላይ ግን ተቀልብሶ የሃኪም ትዕዛዝን በግዴታነት አስቀምጧል።
ዳንኮ እና ጄንባዮፕሮ በተባሉት ኩባንያዎች የሚመረተውን መድሃኒት ፈቃድ በተሰጣቸው የችርቻሮ መድሃኒት አከፋፋዮች ለማቅረብም ከስምምነት ላይ ስለመደረሱ ሮይተርስ አስነብቧል።
አዲሱን ውሳኔ “ትልቅ እርምጃ” ነው ያሉት እንዳሉ ሁሉ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙም አልታጡም።
የጽንስ ማስወረድን የሚቃወመው ኤስ ቢ ኤ የተባለ ተቋም ፕሬዝዳንቷ ማርጆሬ ዳነንፌልሰር፥ “ውሳኔው የበርካታ ሴቶችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤ የግዛቶች ህግ አውጪዎች የባይደን አስተደደርን ጽንስ የማስወረድ ጽንፈኛ እሳቤ ሊቃወሙት ይገባል” ብለዋል።
ድጋፍ የቸሩት የአሜሪካ ተቋማት ደግሞ ውሳኔው ባልተፈለገ መንገድ የሚፈጠር ጽንስን ለማስወረድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው በመጥቀስ የአስተዳደሩን ውሳኔ አሞካሽተውታል።
የውርጃ መብት ተሟጋቾች፥ መድሃኒቱ ደህንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ መሆኑ ለረጅም ጊዜ መታየቱን ያነሳሉ።
በህንድም ሆነ በሜክሲኮ ያለምንም የሃኪም ትዕዛዝ መድሃኒቱ በችርቻሮ መደብሮች እንደሚሸጥና የከፋ ጉዳይ አለማድርሱንም ነው የሚጠቅሱት።
በአሜሪካም ከ2000 ጀምሮ መድሃኒቱን ከ4 ነጥብ 9 ሚሊየን ሰዎች ወስደው በመድሃኒቱ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡት 26 ብቻ መሆናቸውን የአሜሪካ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር መረጃ ያሳያል።
በሀገሪቱ በጽንስ ማስወረድ መብት ዙሪያ ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት ግን አሁንም ድረስ አልረገበም።
ከአስር በላይ የአሜሪካ ግዛቶችም ውርጃን በህግ እንደከለከሉ ናቸው።
በእነዚህ ክልከላው ባለባቸው ግዛቶችም ጽንሳቸውን ማስወረድ የሚፈልጉ ሴቶች ወደተፈቀደባቸው ግዛቶች በመጓዝ ማይፍፕሪስተን የተሰኘውን መድሃኒት ገዝተው መጠቅም ይችላሉ ተብሏል።