ግለሰቡ ላደረሰው ጉዳት የ60 ዓመት እስር እንደሚጠብቀው ተገልጿል
የኮምፒውተር ቫይረሶችን በመጠቀም 6 ቢሊዮን ዶላር የመዘበረው ሰው
ዩንሂን ዋንግ የተባለው የቴክኖሎጂ ባለሙያ በዜግነት ቻይናዊ ሲሆን ከ200 በላይ ሀገራትን በኮምፒውተር ቫይረስ አጥቅቷል፡፡
ቫይረሶችን በመልቀቅ መረጃዎችን ከግለሰቦች እና ተቋማት የሚመነትፈው ይህ ባለሙያ በተለይም የተጠለፉ ኮምፒውተሮችን በመላው ዓለም በማገናኘት ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት ምዝበራ ፈጽሟል ተብሏል፡፡
አሜሪካ ከታይላንድ፣ ሲንጋፖር እና ሌሎች የዓለማችን ሀገራት ጋር በመተባበር ባደረገችው ምርመራ ግለሰቡ በመዘበረው ገንዘብ በተለያዩ ሀገራት ንብረቶችን አፍርቶ ተገኝቷል፡፡
ግለሰቡ በተለያዩ ሀገራት ከ19 ሚሊዮን በላይ የጠለፋቸውን ኮምፒተሮች በማገናኘት 911ኤስ5 የተሰኘ ኮድ በመስጠት ለተለያዩ ተቋማት ያልተፈቀዱ አገልግሎቶችን ሲሰጥ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ይህ ቻይናዊ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ከተለያዩ ግለሰቦች እና ተቋማት መዝብሯል የተባለ ሲሆን የ90 ሚሊዮን ዶላር ንብረቶችን በአምስት ሀገራት ንብረት በስሙ አፍርቶ ተገኝቷል ተብሏል፡፡
ቻይና በ12 የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች
የአሜሪካው ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ ግለሰቡ ያፈራቸውን ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ ከማድረግ ባለፈ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር እንዳዋለው ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪው ለፈጸማቸው ወንጀሎች በበይነ መረብ ጠለፋ፣ ምዝበራ እና ሌሎች የተለያዩ ወንጀሎች ክስ የተመሰረተበት ሲሆን የ60 ዓመት እስር ይጠብቀዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ መንግስትም ተጠርጣሪው ሲጠቀምበት የነበረውን የተጠለፉ ኮምፒውተሮች ኔትወርክ እንዳይሰራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ ከአሜሪካ ውጪ በሲንጋፖር፣ አረብ ኢምሬት፣ ቻይና፣ ታይላድ እና ሌሎችም ሀገራት ያሉት ውድ እና ቅንጡ ንብረቶቹ ታግደዋል ተብሏል፡፡