አሜሪካ በ2024 318.7 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን መሸጧ ተነገረ
የዩክሬን እና የጋዛው ጦርነት የዋሽንግተን የጦር መሳሪያ ንግድ ከ2023ቱ በ29 በመቶ አድጎ ክብረወሰን ሆኖ እንዲመዘገብ አድርገዋል
ቱርክ፣ እስራኤልና ሮማኒያ ቢሊየን ዶላሮችን የሚያወጡ የአሜሪካ የውጊያ ጄቶችና ታንኮችን ገዝተዋል
አሜሪካ በ2024 318.7 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለውጭ ሀገራት መሸጧ ተነገረ።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው አመት የተመዘገበው ሽያጭ ከ2023ቱ በ29 በመቶ አድጎ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
ለዚህም የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ትልቁን ድርሻ ሲይዝ በጋዛ ለ15 ወራት የተካሄደው ጦርነትም አስተዋጽኦ አድርጓል ነው የተባለው።
የአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራቾቹ ሎክሄድ ማርቲን፣ ጀነራል ዳይናሚክስ እና ኖርዝሮፕ ግሩማን ገበያው ደርቶላቸው የጦር መሳሪያዎችን ቸብችበዋል።
በ2024 ከጸደቁ የጦር መሳሪያ ሽያጮች መካከል ቱርክ በ23 ቢሊየን ዶላር "ኤፍ - 16" ጄቶችን ለመግዛትና ለማዘመን የተስማማችበት ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው።
እስራኤል 18.8 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ "ኤፍ -15" ጄቶችን ከአሜሪካ የገዛች ሲሆን፥ ሮማኒያም በ2.5 ቢሊየን ዶላር "ኤም1ኤ2" አብራምስ ታንኮችን ለመግዛት ያቀረበችው ጥያቄ ጸድቋል።
አሜሪካ የጦር መሳሪያዎችን ለውጭ ሀገራት የምትሸጠው በሁለት መንገድ ነው፤ ሀገራት ከጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ጋር በቀጥታ በሚያደርጉት ድርድር እና በመንግስታት በኩል በሚደረግ ንግግር። በሁለቱም መንገዶች ሽያጩ በአሜሪካ መንግስት መጽደቅ ይኖርበታል።
የአሜሪካ ኩባንያዎች ከሀገራት ጋር በቀጥታ በመነጋገር በ2024 200.8 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ሽጠዋል፤ ይህም ከ2023ቱ (157.5 ቢሊየን ዶላር) በ43 ቢሊየን ዶላር ብልጫ ያለው ነው።
በአሜሪካ መንግስት አመቻቺነት የተከናወነው ሽያጭም ከ2023ቱ በ37 ቢሊየን ዶላር ጨምሮ 117.9 ቢሊየን መድረሱን ሬውተርስ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ አስነብቧል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጦር መሳሪያ ሽያጭን "እንደ ወሳኝ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ማስፈጸሚያ እና የረጅም ጊዜ የአለማቀፋዊና ቀጠናዊ ደህንነት ማስጠበቂያ" አድርጎ እንደሚመለከተው ገልጿል።
በቅርቡ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ የገቡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም የአሜሪካ አጋሮች በመከላከያቸው ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈሱ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ትራምፕ ሌሎች የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባላት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸው 5 በመቶውን በመከላከያ ላይ እንዲያውሉ ይፈልጋሉ።