አሜሪካ፤ ሶሪያ በሚገኘው የጦር ሰፈሯ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀች
በጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩ የአሜሪካ ጦር ገልጿል
ጥቃቱ የመጣው "ከኢራን ደጋፊ ታጣቂዎች" ሊሆን ይችላል ተብሏል
አርብ አመሻሽ ላይ በሶሪያ በሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ የሮኬቶች ጥቃት መፈጸሙን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል፡፡
“በሶሪያ አልሻዳዲ በሚገኘው የአሜሪካ የጦር ጣቢያ” ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈጸም በዘጠኝ ቀናት ውስጥ ሶስተኛው መሆኑም ዕዙ ገልጿል፡፡
ቀደም ሲል እንደፈረንጆቹ ህዳር 17 በሶሪያ ትልቁ የነዳጅ ዘይት ቦታ አል ኦማር እና በኢራቅ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የጥምረቱ አረንጓዴ መንደር ጣቢያ ላይ ያነጣጠሩ ሮኬቶች ተተኩሰው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጅ በአሁኑ የሮኬቶች ጥቃት አሜሪካ የምታግዛቸው "የሶሪያ ዲሞክራቲክ ሃይሎች የሮኬት መገኛ ቦታን ጎብኝተው ሶስተኛው ያልተተኮሰ ሮኬት አግኝተዋል" ሲል ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ አመላክተዋል፡፡
በሶሪያ ውስጥ ሰፊ የመረጃ መረብ ያለውና መቀመጫውን በብሪታንያ ያደረገው የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ የሆነ የጦርነት ተቆጣጣሪ፣ ጥቃቱ የመጣው "ከኢራን ደጋፊ ታጣቂዎች" ነው ብሏል።
በጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩም ነው የተገለጸው፡፡
የአሜሪካ ወታደሮች እንደፈረንጆቹ ከ2019 ጀምሮ የእስልምና መንግስት ቡድን (አይኤስ) ከተቆጣጠራቸው የሶሪያ ግዛቶን ጠራርጎ ለመውጣት በመፋለም ላይ የሚገኘውን የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ሃይል (ኤስዲኤፍ) በመደግፍ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
ከአይ ኤስ ቅሪቶች ጋር በሚደረገው ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች አሁንም በሶሪያ ይገኛሉ::