አሜሪካ ቱርክ በኩርዶች ላይ የጀመረችውን ዘመቻ እንድታቆም ጠየቀች
የቱርክ በሶሪያ እና ኢራቅ ወታደራዊ ዘመቻ በአይኤስ ላይ የተጀመረውን ዘመቻ ይጎዳል ተብሏል
ቱርክ የጀመረችው ወታደራዊ ጥቃት ከቀጠለ በእስር ላይ ያሉ ከ10 ሺህ በላይ የአይኤስ ታጣቂዎች ሊያመልጡ እንደሚችሉ ተሰግቷል
አሜሪካ ቱርክ በኩርዶች ላይ የጀመረችውን ዘመቻ እንድታቆም ጠየቀች።
በቱርክ ከሁለት ሳምንት በፊት በደረሰ የሽብር ጥቃትን በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን አሁንም በህክምና ላይ እንዳሉ ተገልጿል።
በፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የሚመራው የቱርክ መንግስት ጥቃቱን ያደረሰው የኩርድ ታጣቂዎች እንደሆኑ የገለጸ ሲሆን የአጸፋ እርምጃ መውሰድም ጀምሯል።
- ቱርክ፤ በኢራቅ እና ሶሪያ ወደ 500 የሚጠጉ የኩርድ ኢላማዎችን መትቻለሁ አለች
- የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን የሶሪያ ወታደራዊ ዘመቻ በአየር ብቻ የተገደበ አይሆንም አሉ
የቱርክ ወታደሮች በሶሪያ እና ኢራቅ በሚገኙ የኩርድ ታጣቂዎች ላይ የሚሳኤል ጥቃት የሰነዘሩ ሲሆን በጥቃቱም ከ500 በላይ ታጣቂዎችን መገደላቸውን አስታውቃለች።
የኩርድ ታጣቂዎች በበኩላቸው የአጸፋ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ተናግረው የቱርክ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ገን የእስላሚክ ስቴት ወይም አይኤስ ታጣቂዎች ጋር የጀመሩትን ውጊያ እንደሚያቆሙ ዝተዋል።
ይሄንን ተከትሎም የአሜሪካ መከላከያ ቢሮ በድረገጹ እንደገለጸው ቱርክ በሶሰሪያ እና ኢራቅ የጀመረችውን ወታደራዊ ጥቃት እንዳሳሰበው ገልጾ አንካራ ጥቃቱን እንድታቆም አሳስቧል።
የአሜሪካ መከላከያ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል ፓትሪክ ሪደር እንዳሉት የቱርክ ጥቃት የኢራቅን እና ሶሪያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ በመሆኑ ጥቃቱ እንዲቆም ጠይቀዋል።
የኩርድ ታጣቂዎች ለዓለም ደህንነት ዋነኛ ስጋት የነበረው የአይኤስኤስ የተሰኘው የሽብር ቡድንን በመዋጋት ረገድ ብዙ አስተዋጽኦ የነበራቸው አሁንም በመዋጋት ላይ እንዳሉም አሜሪካ አስታውቃለች።
የአንካራን የደህንነት ስጋት እንረዳለን የምትለው አሜሪካ የአሁኑ የቱርክ ጥቃት ግን ምክክር ያልተደረገበት እና አይኤስኤስ የሽብር ቡድን መዋጋት ላይ እክል የሚፈጥር እንደሆነ ገልጻለች።
ቱርክ የጀመረችው ጥቃት በዚሁ ከቀጠለ በኩርድ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ያሉ ከ10 ሺህ በላይ የአይኤስኤስ ተጣቂዎች ከእስር ሊያመልጡ እና መልሰው ለአካባቢው ሀገራት ተጨማሪ ስጋት ሊሆኑ እንደሚችሉም የፔንታጎን መግለጫ አሳስቧል።
ቱርክ በኢራቅ በሰነዘረችው የአየር ላይ ጥቃት የአሜሪካ ጦር ማዘዣን ለጥቂት ከጥቃቱ መትረፉ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ የአንካራ ወታደሮች ወደ አካባቢው እንደሚሰማሩ ተገልጿል።