የሜክሲኮው ታዋቂ የእጽ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ “ኤል ማዮ” እና የኤል ቻፖ ልጅ ተያዙ
“ፌንታኒል” የተባለውን አደገኛ እፅ በማምረትና በማሰራጨት ወንጀል የተከሰሱት ግለሰቦች በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት
አደንዛዥ እጹ እድሜያቸው ከ18 እስከ 45 አመት ያሉ አሜሪካውያንን ለሞት በመዳረግ ቀዳሚው መንስኤ መሆኑ ይነገራል
የአለማችን ታዋቂ የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪ ቡድን መሪው ኢስማኤል “ኤል ማዮ” ዛምባዳ እና የቀድሞ አጋሩ “ኤል ቻፖ” ልጅ ዮዋኪን ጉዝማን ሎፔዝ በቁጥጥር ስር ዋሉ።
የሜክሲኮው “ሲናሎዋ” የእጽ አዘዋዋሪ ቡድን አለቃው “ኤል ማዮ” እና የ”ኤል ቻፖ” ልጅ የተያዙት በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ኤል ፓሶ ከተማ ነው።
ግለሰቦቹ ከሳንታ ቴራሳ አውሮፕላን ማረፊያ ከአውሮፕላን ላይ እንደወረዱ መያዛቸው ከመነገሩ ውጭ በቁጥጥር ስር የዋሉበት መንገድ ግን በዝርዝር አልተገለጸም።
የ76 አመቱ “ኤል ማዮ” ዛምባዳ በ2017 በአሜሪካ በቁጥጥር ስር ከዋለው ሌላኛው የአለማችን የአደንዛዥ እጽ ዝውውር መሪ “ኤል ቻፖ” ጋር “ሲናሎዋ” የተሰኘ የወንጀል ቡድን መመስረቱ ይነገራል።
ዛምባዳ “ኤል ቻፖ” ከታሰረ በኋላ እድሜው በ30ዎቹ ውስጥ ከሚገኘው የኤል ቻፖ ልጅ ዮዋኪን ጉዝማን ሎፔዝ ጋር በመሆን ከሄሮይን የበለጠ ሃይል ያለውን “ፌንታኒል” የተሰኘ አደንዛዥ እፅ በማምረትና ወደ አሜሪካ በስፋት በማስገባት በአሜሪካ አቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበት ነበር።
የአሜሪካ መድኃኒት ቁጥጥር ኤጀንሲም ዛምባዳ ያለበትን ለሚጠቁም 15 ሚሊየን ዶላር ጉርሻ ለመስጠት ቃል መግባቱን ሬውተርስ አስታውሷል።
እነ ዛምባዳ በአሜሪካ የሚያዘዋውሩት “ፌንታኒል” እጽ በሀገሪቱ ከ18 እስከ 45 አመት ያሉ ወጣቶችን ለህልፈት በመዳረግ ቀዳሚው መንስኤ መሆኑ ተገልጿል።
“ሲናሎዋ” የተባለው ቡድን አደንዛዥ እጾችን ከ50 በላይ ወደሚሆኑ የአለማችን ሀገራት የሚልክ ሲሆን፥ በሜክሲኮ ከሚገኙ ሁለት የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች አንደኛው መሆኑን የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
መሪው ዛምባዳ በሜክሲኮ በሪል ስቴት ዘርፍ የተሰማራ ሲሆን ሆቴሎች፣ ግዙፍ የወተት ማምረቻ ኩባንያ እና ሌሎች ንብረቶች እንዳሉት ይነገራል።
ይህም የሜክሲኮ ባለስልጣናትን በጉቦ በመደለል እንዳሻው እንዲንቀሳቀስ አድርጎታል ተብሏል።
በአሜሪካ በቁጥጥር ስር የዋሉት የ”ሲናሎዋ” መሪ እና አጋር (የኤል ቻፖ ልጅ) በአደገኛ እጽ ዝውውር፣ በግድያ ወንጀል፣ በእገታና ህገወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀሎች ክስ እንደሚቀርብባቸው ይጠበቃል።