የሐማሱ የፖለቲካ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየሕ መገደላቸውን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ተሰንዝሯል
እስራኤል ከተጠቃች አሜሪካ ገለልተኛ እንደማትሆን አስታወቀች፡፡
ከ10 ወራት በፊት ሐማስ በእስራኤል ምድር ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
በጋዛ የተጀመረው ይህ ጦርነት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ወደ ሊባኖስ እና የመን እየተስፋፋ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ በሌሎች አካባቢዎችን ሊሰፋ እንደሚችል ስጋት አይሏል፡፡
በተለይም በኢራን ተመራጩ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት ወደ ቴህራን ያመሩት የሐማሱ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ መገደል ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሯል፡፡
ግድያው በግዛቷ የተፈጸመባት ኢራን እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች፡፡
የእስማኤል ሀኒየህ ግድያ እንዲፈጸም ተሳትፎም ሆነ እውቅና የለኝም ያለችው አሜሪካ ኢራን እስራኤል ካጠቃች ግን ገለልተኛ እንደማትሆን አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊዮልድ ኦስቲን ከእስራኤል አቻቸው ዮአቭ ጋላንት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በስልክ እንደተወያዩ ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ በሐማሱ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ግድያ ላይ እጄ የለበትም አለች
እንደዘገባው ከሆነ ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመች አሜሪካ ገለልተኛ እንደማትሆን ሚኒስትሩ መናገራቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህን ተከትሎም ኢራን እና አጋሮቿ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ በሚል አሜሪካ የአየር ላይ ጥቃቶችን ማክሸፊያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ወደ አካባቢው መላኳን አስታውቃለች፡፡
የእስራኤል -ሐማስ ጦርነት እንደተጀመረ ሰሞን ኢራን እና ሌሎችም ሀገራት አሜሪካ ጣልቃ እንዳትገባ አስጠንቅቀው የነበረ ቢሆንም ዋሸንግተን በግልጽ ለእስራኤል ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡
ኢራን ከእስራኤል ጋር የቀጥታ ጦርነት እንዳይጀምሩ የተሰጋ ሲሆን የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ በበኩሏ የእስማኤል ሀኒየህ ግድያን አውግዛለች፡፡
ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶሀን ሀገራቸው በሊቢያ እና አዛርባጂያን ያደረገችውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በጋዛም ልታደርግ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል፡፡