ኢትዮጵያ በሰላም ስምምነቱ ላይ እያስመዘገበች ያለው ስኬት በአሜሪካ እውቅና ማግኘቱን መንግስት ገለጸ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት አንቶኒ ብሊንከንን ተቀብለው አነጋግረዋል

በኢፌዴሪ መንግስት እና ህወሃት መካከል በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ ሚና አንደነበራት ይታወሳል
ኢትዮጵያ በሰላም ስምምነቱ ላይ እያስመዘገበች ያለችው ስኬት በአሜሪካ እውቅና ማግኘቱን መንግስት ገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ረፋድ ላይ የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት አንቶኒ ብሊንከንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከብሊንከን ጋር የነበራቸው ውይይት በተለያዩ የሀገር ውስጥ፣ ቀጣናዊ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማምተዋል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።
- ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በመንግስትና በህወሓት መካከል ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ምን አሉʔ
- ውይይቱ “የሰላም ስምምነቱ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል” የሚል መንፈስ ፈጥሯል - አምባሳደር ወንድሙ
በኢኮኖሚው፣ በልማት ጥረቶች፣ በተለይም በግብርና እና በቀጣናዊ መረጋጋት ላይ ያሉ ጉዳዮችም በውይይቱ ትኩረት የተሰጠባቸው ናቸው።
በህወሓት እና መንግስት መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ ሚና አንደነበራት ይታወሳል።
ሁለት አመት ያስቆጠረውን ጦርነት ማስቆም የቻለውን ስምምነት በተለያዩ ጊዜያት ያደነቀችው አሜሪካ፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ተጠያቂነት መስፈን እንደሚገባ ስትገልጽም ቆይታለች።
የኢትዮጵያ መንግስት በሽግግር ፍትህ አማካኝነት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች መፍትሄ እንደሚያገኙ በመግለጽ ላይ መሆኑ ይታወቃል።
መንግስት ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከተመድ ጋር በትብብር የሰራውን የምርመራ ውጤት ከተወሰኑ ነጥቦች ውጭ ያሉትን እንደሚቀበል እና ተጠያቂነት ለማስፈን እንደሚጠቀምበት መግለጹም ይታወሳል።
ነገርግን ኢትዮጵያ የተመድን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ጥሰት መርማሪ ባለሙያዎች የፖለቲካ አላማ ያላቸው ናቸው በማለት በአዎንታ አትመለከታቸውም።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ የባለሙያዎች ቡድኑ የቆይታ ጊዜው እንዳይራዘም እና እንዲበተን መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።
በተቃራኒው ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች የባለሙያዎቹ የስራ ጊዜ እንዲራዘም እና ኢትዮጵያም እንድትቀበል ጫና እየፈጠሩ ነው።