የመንግስትና የህወሓትን የሰላም ስምምነት የሚቆጣጠርና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን ተቋቋመ
የኬንያ፣ የናይጄሪያ እና የደቡብ አፍሪካ ወታደራዊ አመራሮች የተልእኮ ቡድኑ አባላት ሆነው ተመድበዋል
የተልዕኮ ቡድኑ የፌደራል ፖሊስ በመቀሌ ከተማ ያሉ የመንግስት ተቋማትን የማረካከብ ሂደትን አስፈጽመዋል
በአፍሪካ ሕብረት ስር የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር የተልዕኮ (Mission) ቡድን ተቋቋመ።
የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን በሰላም ስምምነቱ የተጠቀሱ ነጥቦች ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ በዛሬው እለት መቀሌ መግባ ይታወቃል።
ታዛቢ ቡድኑ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በተገኙበት ስብስባውን ያደረገ ሲሆን፤ የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን አቋቁሟል።
በአፍሪካ ህብረት ስር የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከበር የተልዕኮ ቡድኑ ሶስት አባላት ያሉት ሲሆን በሰላም ስምምነቱ መሰረት የሲቪልና ወታደራዊ ስምምነቱን አፈፃፀም የሚከታተል መሆኑን ኢ.ዜ.አ ዘግቧል።
የተልዕኮ ቡድኑ አባልነትም ሜጀር ጀነራል ራዲና ስቴፈን ከኬንያ፣ ኮሎኔል ሩፋይ ኡመር ማይሪጋ ከናይጄሪያ እንዲሁም ኮሎኔል ቴፎ ሰኮል ከደቡብ አፍሪካ ተሰይመዋል።
አባላቱ በዛሬው እለት የፌደራል ፖሊስ በመቀሌ ከተማ ያሉ የመንግስት ተቋማትን የማረካከብ ሂደትን ማስፈጸማቸውም ተነግሯል።
በዚህ ወቅት የተልዕኮ ቡድኑ ሀላፊ ሜጀር ጀነራል ራዲና ስቴፈን የሰላም ስምምነቱን አፈፃፀም ለመረዳት ጠቃሚ መንገድ ነው ማለታቸውን ኢዜአ በዘገባው አክሏል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት በፌደራል መንግስት መንግስት የሚተዳደሩ ተቋማትን ለመጠበቅ በዛሬው እለት መቀሌ መግባቱ ይታወቃል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከቀናት በፊት በትዊተር ገታቸው በሳፈሩት ጽሁፍ፤ በ2ኛው የናይሮቢ የሰላም ስምምነት መሠረት ህወሓት የታጠቃቸው ከባባድ የጦር መሳሪያዎችን ለመንግስት የማስረከብ ስራ እስከ ሀሙስ እንደሚከናወን መግለጻው ይታወሳል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በመቀሌ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን በሰላም ስምምነቱ የተጠቀሱ ነጥቦች ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ በዛሬው እለት መቀሌ ገብተዋል።
በያዝነው ሳምንትም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ የፌደራል መንግስ ልዑክ ወደ መቀሌ ማቅናቱም አይዘነጋም።