ውይይቱ “የሰላም ስምምነቱ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል” የሚል መንፈስ ፈጥሯል - አምባሳደር ወንድሙ
የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ተብሏል
አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሟላ የትራንስፖርት እና ባንክ አገልግሎት እንዲጀመር ውሳኔ አሳልፈዋል ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከመንግስት እና ህወሓት ሰላም ስምምነት ትግበራ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ጋር በሐላላ ኬላ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የተፈረመው የዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ሁለት አመት ያስቆጠረውን ጦርነት አስቁሟል።
ውይይቱ ከተፈረመ ድፍን ሶስት ወር የሆነው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የእስካሁኑ አፈጻጸም የተገመገመበት እንደነበር የህወሓት ተደራዳሪ ቡድን አባል የሆኑት አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው ለአል-ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ከሆነ፤ የስምምነቱ አፈጻጸም አልፎ አልፎ መዘግየት ቢታይበትም በተስማማነው መሰረት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡
የውይይቱን ዝርዝር ጉዳዮች በተለይም ከወታደራዊ እና ደህንነት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ነጥቦች ከመናገር የተቆጠቡት አምባሳደሩ ውይይቱ በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ የተቀመጠበት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
“የባንክ አገልግሎት፣ የየብስ ትራንስፖርት እንዲሁም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ማቋቋም የሰላም ኮሚቴው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆኑ አቅጣጫ ያስቀመጠባቸው ናቸው”ም ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
አምባሳደሩ፤ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ ስለመኖሩ ግን በግልጽ ያሉት ነገር የለም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አህመድ ከአየር ትራንስፖርት ፣ባንክ እና ሌሎች አመኔታን የሚያጎለብቱ እና የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት የሚያቃልሉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፋቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን በትዊትር ገጻቸው አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ከህወሓት ተደራዳሪ አባለት ጋር በአካል ተገናኝተው ሲነጋገሩ ይህ የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡
አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው፤ ሁለት አመት ከፈጀው ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ደራጃ ከህወሓት አመራሮች ጋር በአካል ተገናኝቶ መወያየት ሁለቱም አካላት ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝት የሚያሳይ ብለዋል፡፡
ውይይቱ በሁለታችን በኩል “የሰላም ስምምነቱ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል የሚል መንፈስ የፈጠረ ነው” ሲሉም ነው የተማገሩት የህወሓት ተደራዳሩ ቡድን አባሉ አምባሳደር ወንድሙ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በተካሄደው የመጀመሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ አስተባባሪ ኮሚቴ ውይይት ላይ በፌደራል መንግስት በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን እና ኢታማዦር ሹሙን ጨምሮ ሌሎች የተደራዳሪ ቡድኑ አባላት ተገኝተዋል፡፡
በህወሓት በኩልም አቶ ጌታው ረዳ፣ ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ ጄነራል ጻቃን እና ሌሎችን የህወሓት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡