የህወሓት ትጥቅ ማምረቻና ማሠልጠኛ ዒላማ ያደረጉ የአየር ድብደባዎችን መፈጸሙን መንግስት አስታወቀ
የአየር ድብደባው ከሰኞ ጀምሮ የቀጠለ ሲሆን የዛሬው ለ5ኛ ጊዜ መሆኑ ይታወቃል
የአየር ድብደባው በማይጠብሪ እና ዐድዋ አካባቢ ማካሄዱን መንግስት አስታውቋል
የህወሓት ማሠልጠኛና ወታደራዊ ትጥቅ ማምረቻዎችን ዒላማ ያደረገ የአየር ድብደባ መፈጸሙን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ ሰላማዊ ካሳ የአየር ድብደባ መካሄዱን ለአል ዐይን አረጋግጠዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትም በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ “ዛሬ በምእራብ ግንባር የጠላት ማሠልጠኛ እና የሰው ኃይል ማደራጃ የሆነው ማይጠብሪ በአየር ተመቷል” ብሏል።
በተጨማሪም “ዛሬ ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓም፣ ዐድዋ አካባቢ የሚገኘው፣ ጠላት ወታደራዊ ትጥቅ እና ወታደራዊ አልባሳትን አመሳስሎ የሚያመርትበት ማዕከል በአየር ድብደባ ከጥቅም ውጭ ሆኗል” ሲልም አስታውቋል።
- የህወሓትን የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ዒላማ ያደረገ የአየር ድብደባ መፈጸሙን መንግስት አስታወቀ
- ዛሬ የህወሓትን የጦር መሳሪያ ማምረቻዎች በአየር መደብደቡን መንግስት አስታወቀ
መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ባሳለፍነው አርብ በገጹ ባወጣው መግለጫ “የህወሓት ማሰልጠኛ ማዕከል የአየር ጥቃት ዒላማ ሆኗል” ማለቱ ይታወሳል
ማዕከሉ “ለህወሓት ቡድን ወታደራዊ ሥልጠና ከመዋሉ በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ማሠልጠኛ ማዕከል” እንደነበርም ነው በማጣሪያ ገጹ የሰፈረው።
የኢትዮጵያ አየር ሀይል ካሳለፍነው ሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምሮ በመቀሌ እና አካባቢው የአየር ድብደባዎች መፈጸማቸውን መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል።
መንግስት ለሀገር ስጋት ችግር ይፈጥራል ያለውን ጉዳይ በየትኛውም ሰዓት እና በማንኛውም ሁኔታ ንጹሃን ዜጎችን በጠበቀ መልኩ ሊመታ እንደሚችል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለአል ዐይን መናገራቸውም አይዘነጋም።