ሕወሓት የጀመረውን ሀገር የማውደምና የማፍረስ ተልዕኮ በመደበኛ ወታደራዊ አደረጃጀት ብቻ መቀልበስና መቅበር እንደማይቻል ገልጿል
በአሸባሪነት ተፈረጀው ሕወሓት የሚፈጽመውን የሽብር ተግባር ለመቀልበስ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ዛሬ ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ/ም በባህርዳር ምክክር ያደረገው ሀገር-አቀፉ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የህግ አስፈፃሚዎች የግንኙነት መድረክ በድጋሚ የህዝባዊ ዘመቻ ጥሪ አቀረበ፡፡
የግንኙነት መድረኩ ሁኔታውን የተመለከተ ዝርዝር መግለጫ አውጥቷል፡፡
“ሰራዊቱ አስፈላጊ ሲሆን እጅን በአፍ ላይ ለሚያስጭን ተልዕኮ ዝግጁ ነው”- ጠ/ሚ ዐቢይ
በመግለጫው ሕወሓት የጀመረውን ሀገር የማውደምና የማፍረስ ተልዕኮ በመደበኛ ወታደራዊ አደረጃጀት ብቻ መቀልበስና መቅበር አይቻልም። ያለው የግንኙነት መድረኩ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በማነቃነቅና ባለቤት በማድረግ የአገርን ህልውና ከሁሉ አቀፍ ጥቃት መከላከል ያስፈልጋል ብሏል፡፡
የምንከተለው የዘመቻ ስልት የሽብር ቡድኑን ዐቅምና የክፋት ምኞቱን በመስበር አገር የማፍረስ ህልሙን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማምከን መሆን አለበት ሲል በመግለጫው ያተተው፡፡
ሕወሃት የኢትዮጵያ የወቅቱ አንደኛ፣ አደገኛና ቀንደኛ የደኅንነት ሥጋት ነው ሲልም አስቀምጧል።
መግለጫው የዚህን የጥፋት ቡድን ተልዕኮ ለመቀልበስ፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ ሆነን መነሣት አለብን የሚልም ሲሆን የሚያጋጥመንን ሕመም ችለን፤ የሚደቀንብንን ፈተና ተቋቁመን፣ የውስጥ ክፍተቶቻችንን ሞልተን፣ ጠንክረንና ነጥረን በመውጣት የጥፋት ቡድኑን ምኞት እናመክናለንም ይላል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የክተት ጥሪ አስተላለፉ
የኢትዮጵያ መከራ የሆነ ጠላት ያለው ህወሓት እንዴት በሕዝባዊ ኃይል ተመክቶና ተቀልብሶ እንደሚደመሰስ መክረናል የሚለው መግለጫው የጥፋት ቡድኑን ተልዕኮ በአነስተኛ መሥዋዕትነት ለማምከን ዝግጁነታችንን ደግመን አረጋግጠናል ሲል ይገልጻል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጦርነቱን ስፋትና ጥልቀት በመረዳት እንደወትሮው ሁሉ ከሰራዊቱና ከሁሉም ክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ አገሩን ከጥቃት እንዲከላከልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በውጭ የሚኖሩትን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሚቀርብላቸው ማንኛውም አገራዊ ግዴታ ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያን ለማዳን እንዲዘምቱም ሲልም ነው ጥሪውን ያስተላለፈው፡፡