በዩክሬን የሚገኙ አፍሪካዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት የመሄድ መብታቸው እንዲከበር አፍሪካ ህብረት አሳሰበ
ህብረቱ በዩክሬን የሚገኙ አፍሪካዊያንን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል
አፍሪካዊያን በግጭት ወቅት የዓለም አቀፍ ድንበሮችን የማቋረጥ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል ተብሏል
በዩክሬን የሚገኙ አፍሪካዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት የመሄድ መብታቸው እንዲከበር አፍሪካ ህብረት አሳሰበ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባት ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ያመሩ ሲሆን ጦርነቱ ከተጀመረ ዛሬ ስድስተኛ ቀናቸው ላይ ነው።
እስካሁን ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች ዩክሬንን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሲሆን፤ በዩክሬን ከተሞች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አፍሪካዊያን የተለያዩ እንግልቶች እየደረሱባቸው መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተለቀቁ የተንቀሳቃሽ ምስሎች ያስረዳሉ።
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሆኑት የሴኔጋሉ ፕሬዘዳንት ማኪ ሳል እና የህብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሃማት በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ በዩክሬን ያሉ ሁኔታዎችን በመከታተል ላይ ነን ብለዋል።
በተለይም በዩክሬን የሚኖሩ አፍሪካዊያን ደህንነት እንዳሳሰበው የገለጸው የአፍሪካ ህብረት አፍሪካዊያን እንደማንኛውም ዜጋ ወደ ጎረቤት ሀገራት የመግባት መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል ሲልም አሳስቧል።
በተለይም በግጭቶች እና የጦርነት ወቅቶች ለደህንነታቸው የሰጉ ዜጎች የሀገራትን ዓለም አቀፍ ድንበሮች አቋርጠው የመግባት መብት እንዲከበርም ህብረቱ በመግለጫው አሳስቧል።
በዩክሬን የሚኖሩ አፍሪካዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመሄድ ሲሞክሩ በዩክሬናዊያን የደረሰባቸው እንግልት ግልጽ የዘረኝነት ጥቃት በመሆኑ ድርጊቱ ሊቆም እንደሚገባም ተገልጿል።
በዩክሬን የሚገኙ አፍሪካዊያንን ደህንነት ለማስጠበቅ የህብረቱ አባል ሀገራትን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም የህብረቱ መግለጫ ያስረዳል።
ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡበትን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት በቤላሩስ ትናንት የመከሩ ቢሆንም ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ውይይታቸውን ከሁለት ቀን በኋላ ዳግም ለመጀመር ተስማምተዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን የዩክሬን መዲና ኬቭን ለመቆጣጠር የሩሲያ ወታደሮች በውጊያ ላይ ሲሆኑ በሩሲያ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች ግን እንደቀጠሉ ናቸው።