ክትባት እና ኦቲዝም ባላቸው ዝምድና ላይ ጥናት ሊደረግ ነው
አሜሪካ ክትባቶች ለኦቲዝም መነሻ ይሆናሉ? በሚለው ጉዳይ ዙሪያ አዲስ ጥናት እንዲደረግ አዛለች

በመላው ዓለም በኦቲዝም የሚጠቁ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም እስካሁን ትክክለኛው ምክንያት አልታወቀም
ክትባት እና ኦቲዝም ባላቸው ዝምድና ላይ ጥናት ሊደረግ ነው፡፡
የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ወይም ሲዲሲ በክትባት እና ኦቲዝም ዙሪያ አዲስ ጥናት ሊያካሂድ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር በቅርቡ በክትባት ተጠራጣሪነታቸው የሚታወቁት ሮበርት ኬነዲ ጁኒየርን የጤና መምሪያ ሃለፊ አድርገው መሾማቸው ይታወሳል፡፡
እኝህ ፖለቲከኛ ከጠየና ጋር የተያያዙ ስራዎችን ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ጨምሮ ሌሎችንም ክትባቶችን ለመውሰድ ሲቃወሙ ነበር፡፡
በተለይም ለህጻናት የበሽታ መከላከል አቅማቸውን ለማሳደግ በሚል የሚሰጡ ክትባቶች በአእምሮ እድገት ውስንነት ወይም ኦቲዝም የሚጠቁ ህጻናት ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ናቸው በሚል አቋማቸው ይታወቃሉ፡፡
እኝህ ፖለቲከኛ ስልጣን በያዙ በአንድ ወር ውስጥ ክትባቶች እና ኦቲዝም ያላቸው ዝምድና ካለ ወይም ክትባቶች ለኦቲዝም መነሻ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ አዲስ ጥናት እንዲደረግ ስለማቀዳቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ጥናቱ ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል የተባለ ሲሆን በትክክል መቼ እንደሚጀመር በዘገባው ላይ አልተጠቀሰም፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ላይ በአሜሪካ በቅርቡ ከ10 ሺህ ህጻናት መካከል አንዱ በኦቲዝም ይጠቃ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ከ36 ህጻናት ውስጥ አንዱ በኦቲዝም ይጠቃል፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ መጠናት እና መታወቅ አለበት ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ክትባቶች መሰጠቱ ከ154 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ይሞቱ ነበር ብሏል፡፡
ክትባቶች ለኦቲዝም መነሻ ናቸው የሚለው ሀሳብ የተነሳው ከ27 ዓመት በፊት በአንድ የብሪታንያው ሐኪም አንድሪው ወክፊልድ አማካኝነት ቢሆንም ይህ ሐኪም በሀገሪቱ ባሉ የሕክምና ስራዎች ዙሪያ እንዳይሳተፍ እገዳ ተጥሎበታል፡፡