በአሜሪካ ላይ የበይነ መረብ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ ሰዎች የ75 ሺህ ዶላር ቅጣት ተጣለባቸው
በቻይና መንግስት ይደገፋሉ የተባሉ የበይነ መረብ መንታፊዎች የአሜሪካ ተቋማትን እና ዜጎችን ኢላማ አድርገው ነበር ተብሏል

አሜሪካ ቅጣቱን በ12 ቻይናዊያን ላይ ጥላለች
በአሜሪካ ላይ የበይነ መረብ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ ሰዎች የ75 ሺህ ዶላር ቅጣት ተጣለባቸው፡፡
የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር እንደገለጸው በቻይና የሚደገፉ የበይነ መረብ መንታፊዎች የተለያዩ ተቋማትን እና ግለሰቦችን ኢላማ አድርገው ቆይተዋል ብሏል፡፡
ሀገሪቱ በተለይም መሰረቱን በቻይና ያደረገ እና በመንግስት ይደገፋል የሚባለው አይ-ሱን የተሰኘው የበይነ መረብ መረጃ መንታፊ ቡድን ባለሙያዎችን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እንደምትከፍል ከዓመታት በፊት ገልጻ ነበር፡፡
ለዓመታ በተደረገው ምርመራ ይህ ቡድን የአሜሪካ ተቋማትን፣ የቻይና መንግስትን ይተቻሉ የተባሉ ፖለቲከኞች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና ሚዲያዎች የጥቃቱ ኢላማ ሆነው ቆይተዋል ተብሏል፡፡
በነዚህ አካላት ላይ መረጃዎችን የመነተፉ አካላት በቻይና መንግስት ሽልማት ሳይቀር ይሰጣቸው እንደነበርም ቢቢሲ በዘገባው ላይ ጠቅሷል፡፡
በዚህ ስራ ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ቻይናዊያን ለፈጸሙት ወንጀል ከ10 ሺህ እስከ 75 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ተገልጿል፡፡
ቻይና በአሜሪካ በሚቀርብባት ተደጋጋሚ የመይነ መረብ ጥቃት እና ቴክኖሎጂ ስርቆት ክስ አንዱንም ያልተቀበለች ሲሆን የአሁኑን ስለመቀበሏ በዘገባው ላይ አልተጠቀሰም፡፡
አሜሪካ እና ቻይና እርስ በርሳቸው በመረጃ ምንተፋ እና ቴክኖሎጂ ስርቆት የሚወነጃጀሉ ሲሆን የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ቻይናን ሲከሱ ይደመጣሉ፡፡
ለአብነትም በቅርቡ ይፋ የሆነው ዲፕ ሲክ የተሰኘው የኤአይ ሞዴል የተወሰኑ መረጃዎች ከአሜሪካ ኩባንያዎች የተቀዱ መሆናቸው ሲገለጽ ነበር፡፡