የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር በድጋሚ በጠና ታመው ወደ ሆስፒታል ገቡ
ሊዮድ ኦስቲን ከአንድ ወር በፊት ነበር ከጽኑ ህክምና ክትትል አገግመው ወደ ስራቸው የተመለሱት
የካንሰር ህመም ተጠቂ የሆኑት ሚኒስትሩ በድጋሚ ወደ ጽኑ ህክምና ክትትል ገብተዋል ተብሏል
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር በድጋሚ ወደ ሆስፒታል ገቡ፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊዮድ ኦስቲን በፈረንጆቹ 2024 አዲስ ዓመት ላይ በድንገት ታመው ሆስፒታል ገብተው ነበር፡፡
ሚንስትሩ በዚህ ጊዜ በጸና ታመው ለአራት ቀናት የጽኑ ህክምና ክትትል ውስጥ በቆዩባቸው ቀናት ፕሬዝዳንት ባይደንን ጨምሮ ለሀገሪቱ ዋና ዋና ባለስልጣናት አልተናገሩም በሚል ስልጣን እንዲለቁ ሲጠየቁ ከርመዋል፡፡
ግፊቱ እየጨመረ ሲመጣም ህክምናውን ለሚንስትሩ የሰጠው ዋልተር ሪድ ሆስፒታል ሊዮድ ኦስቲን በፕሮስቴት ካንሰር መጠቃታቸውን እና ህክምና እንዳደረገላቸው ይፋ አድርጓል።
የ70 ዓመቱ ጡረተኛው የአሜሪካ ባለ አራት ኮኮብ ጀነራል ሊዮድ ኦስቲን በካንሰር መጠቃታቸውን በወቅቱ የነበረውን ህክምና አጠናቀው ወደ ስራቸው እንደተመለሱ በተነገረ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በድጋሚ በጠና ታመው ሆስፒታል መግባታቸውን ፔንታጎን ይፋ አድርጓል፡፡
ሚኒስትሩ ከጣፊያ ጋር በተያያዘ የነበረባቸው ህመም አገርሽቶባቸው በዚሁ ሆስፒታል የጽኑ ህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ እና ሚኒስትሩ ስራቸውን ለምክትላቸው አሳልፈው ሰጥተዋልም ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ካትሊን ሂክስ የሊዮድ ኢስቲን ሃላፊነትን ተረክበው ስራ እየሰሩ ነው የተባለ ሲሆን በተለይ ከዩክሬን፣እስራኤል፣ ቀይ ባህር እና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን እንደሚመሩም ተገልጿል፡፡
ሚኒስትሩ ሊዮድ ኦስቲን በዚህ ሳምንት ውስጥ ወደ ኪቭ አምርተው ከዩክሬን ወታደራዊ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ የሚል ቀጠሮ ይዘው ነበር ተብሏል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ አባል የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት የሚጠበቅባቸውን ዓመታዊ መዋጮ ካላዋጡ ሀገራቸው በማንኛውም አካል ከሚደርስባቸው ጥቃት የመከላከል ግዴታ የለባትም ማለታቸው አውሮፓዊያንን አስደንግጧል፡፡