ለቀናት ተደብቀው በጽኑ ህክምና ክትትል ውስጥ የቆዩት ሚንስትሩ ስልጣን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ነው
የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ሊዮድ ኦስቲን በካንሰር መጠቃታቸው ተገለጸ።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊዮድ ኦስቲን ባሳለፍነው ሳምንት በጸና ታመው ሆስፒታል መግባታቸው ይታወሳል፡፡
ሚንስትሩ በጸና ታመው ለአራት ቀናት የጽኑ ህክምና ክትትል ውስጥ በቆዩባቸው ቀናት ፕሬዝዳንት ባይደንን ጨምሮ የሀገሪቱ ዋና ዋና ባለስልጣናት እንደማያውቁም ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ሚንስትሩ ያጋጠማቸው ህመም ምን እንደሆነ ለመንግሥታቸው እና ለህዝብ ሳይነገር መቆየቱ አሜሪካዊያንን ማስቆጣቱ ተገልጿል።
ግፊቱ እየጨመረ ሲመጣም ህክምናውን ለሚንስትሩ የሰጠው ዋልተር ሪድ ሆስፒታል ሊዮድ ኦስቲን በፕሮስቴት ካንሰር መጠቃታቸውን እና ህክምና እንዳደረገላቸው ይፋ አድርጓል።
የ70 ዓመቱ ጡረተኛው የአሜሪካ ባለ አራት ኮኮብ ጀነራል ሊዮድ ኦስቲን በካንሰር መጠቃታቸውን ፕሬዝዳንት ባይደን ሳይቀር እንደማያውቁ ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህን ተከትሎም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች ሊዮድ ኦስቲን ሀላፊነታቸው አልተወጡም፣ ስልጣን ሊለቁ ይገባል ብለዋል።
አሜሪካ በኢራቅ ያደረገችውን ዘመቻ የመሩት ጀነራል ኦስቲን የመጀመሪያው ጥቁር መከላከያ ሚንስትርም ናቸው።
ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮም ከፕሮስቴት ካንሰር ህመም ባለፈ የአንጀት እክል፣ እግራቸውን እና ሌሎች የሰውነታቸው ክፍል ላይ ከባድ ህመም አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል አምርተው ለቀናት በማደንዘዣ ውስጥ ቆይተዋል ተብሏል።
ሚንስትሩ እስካሁን ፔንታጎን ወደ ሚገኘው ቢሯቸው ያልተመለሱ ሲሆን መቼ እንደሚመለሱም አልተገለጸም።
አሜሪካ በኢራቅ፣ እስራኤል እና ዩክሬን ያሉ ጦርነቶች በየጊዜው ሁኔታዎች የሚቀያየሩ በመሆኑ መከላከያ ሚንስትሩ ትኩረታቸው እነዚህ ቦታዎች ላይ ሊሆን ይገባል በሚል ስልጣን እንዲለቁ ግፊቱ ቀጥሏል።
እንደ አሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ገለጻ ከሆነ የሊዮድ ኦስቲን መታመም ለፕሬዝዳንቱ ያልተነገረው ሚኒስትሩ መታመማቸው በሚዲያ እና ለማንኛውም ባለስልጣን እንዳይነገር በመፈለጋቸው ነው፡፡