አሜሪካ የሩሲያውን ተዋጊ ቡድን ዋግነር ግሩፕን “ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ ቡድን” አድርጋ ልትፈርጅ ነው
ዋግነር ግሩፕ ከሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ማስገባት መጀመሩ ዋሽንግተንን እንዳስቆጣት ይነገራል
50ሺህ ያህሉ የቅጥረኛ ቡድኑ ዋግነር ቡድን ተዋጊዎች በዩክሬን ጦርነት በመሳተፍ ላይ ናቸው ተብሏል
አሜሪካ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቅጥረኛ ተዋጊዎቹን በዩክሬን ጦርነት እንዳሳተፈ የሚነገርለትን የሩሲያውን ተዋጊ ቡድን ዋግነር ግሩፕን “ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ ቡድን” አድርጋ ልትፈርጅ እንደሆነ አስታወቀች፡፡
በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የድጋፍ አውታሮቹ ላይ በሚቀጥለው ሳምንት ማዕቀብ እንደምትጥል ዋይት ሃውስ ገልጿል፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ኪርቢ ለጋዜጠኖች በሰጡት መግለጫ ዋግነር ግሩፕ “በዩክሬን እና ሌሎች አከባቢዎች ላይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየፈጸመ ነው” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 50 ሺህ ያህሉ የቅጥረኛ ቡድኑ ተዋጊዎች በዩክሬን ጦርነት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውም ተናግረዋል ቃል አቀባዩ፡፡
አዲሱ እርምጃ አሜሪካ በሶሪያ፣ ሊቢያ፣ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ሌሎች የዓለም ክፍሎች በሚንቀሳቀሰው ቅጥረኛ የተዋጊወች ዋግነር ቡድን ላይ መጠነ ሰፊ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ቃል አቀባዩ ኪርቢ እንዳሉት በዩክሬን ላይ ከተሳተፉ የቡድኑ ወታደሮች 80 በመቶ የሚሆኑት ከየእርስ ቤቶች የተመለመሉና የተወሰዱ ናቸው፡፡
ቅጥረኛ ቡድኑ አሁን ላይ ከመደበኛው የሩሲያ ጦር ጋር ውጥረት ውስጥ መግባቱን የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ ፑቲን ሳይቀሩ ከመደበኛ ጦራቸው የበለጠ እምነት እያሳደሩበት ያለ ኃይል መሆኑም ተናግረዋል፡፡
የዋግነር ግሩፕ መሪው የቭገኒ ፕሪጎዥን ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ያለው ትስስር ውጥረቱ እጅጉን እንዲባባስ እንዳደረገውም ጭምር ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የዋግነር ቡድን ሰዎች የያዙ የሩሲያ ባቡሮች ወደ ሰሜን ኮሪያ ተጉዘው ለቡድኑ ታጣቂዎች የሚሆኑ ሮኬቶችና ሚሳይሎች ይዘው መመለሳቸው የአሜሪካ የስለላ ተቋም በምስልም ጭምር የታገዘ ማስረጃ እንዳለው ቃል አቀባዩ መናገራቸው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
“ዋግነርን የሚደግፉ አካላት ማንነት ለማወቅና በዓለም መድረክ ለማጋለጥ ያለእረፍት እንሰራለን” ሲሉም አክለዋል፡፡
አሜሪካ፤ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የሚደረገው የጦር መሳሪያ ዝውውር የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ የሚጥስ መሆኑ ታምናለች ያሉት ቃል አቀበዩ፤ ማስረጃዋን “ለተመድ የሰሜን ኮሪያ ማዕቀብ ኮሚቴ አጋርታለችም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ አስተያየት ዙሪያ በዋግነር ግሩፕ መሪው ፕሪጎዥን በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡