ታዋቂው የአሜሪካ ዲፕሎማት ሄነሪ ኪሲንጀር በ100 አመታቸው አረፉ
አሜሪካን ከቻይና እና ሶቪየት ህብረት ጋር ያቀራረቡት ጉምቱ ዲፕሎማት አወዛጋቢ የኖቬል ሽልማት መውሰዳቸው ይታወሳል
ኪሲንጀርን የሚያወድሷቸው እንዳሉ ሁሉ በጦር ወንጀለኛኝነት የሚከሷቸውም ጥቂት አይደሉም
ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መልክ ያስያዙ በሚል የሚወደሱት ሄነሪ ኪሲንጀር በ100 አመታቸው ህይወታቸው አለፈ።
ኪሲንጀር በኮኔክቲከት በሚገኝ ቤታቸው ውስጥ ህይወታቸው ማለፉ መገለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
በ1970ዎቹ የአሜሪካ ብሎም የአለም ሀገራትን ግንኙነት ቀይረዋል የሚባልላቸው ዲፕሎማት አሜሪካ ከቻይና ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንድትጀምር አድርገዋል።
አሜሪካ እና የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት የኒዩክሌር መሳሪያ ፉክክርን ለማቆም ስምምነት ላይ ሲደርሱም ሄነሪ ኪሲንጀር ቁልፍ ሰው ነበሩ።
በጀርመን ከአይሁዳውያን ወላጆቻቸው የተወለዱት ሄንዝ አልፈርድ ኪሲንጀር (ሄነሪ ኪሲንጀር) እስራኤል ከአረብ ሀገራት ጋር ግንኙነት እንድትጀምር በማድረግም ስማቸው ይወሳል።
የቬትማኑ ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በ1973 በፓሪስ የተደረሰውን ስምምነት በማርቀቅም የእኝህ ዲፕሎማት ድርሻ ትልቅ መሆኑን ነው ሲኤንኤን ያስታወሰው።
ኪሲንጀር በሪፐብሊካኑ ሪቻርድ ኒክሰን የስልጣን ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው ሰርተዋል።
ከ1974ቱ የዋተርጌት ቅሌት በኋላ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀያሽነታቸው እየደበዘዘ ቢሄድም ኒስከንን በተኩት ጀራልድ ፎርድ ጊዜምየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ሄነሪ ኪሲንጀር በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቅነታቸው በርካቶች ቢያወድሷቸውም በጦር ወንጀለኝነት የሚከሷቸውም ጥቂት አይደሉም።
በተለይ በላቲን አሜሪካ ጸረ ኮሚዩኒስት የሆኑ ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣዎችን መደገፋቸው ያስወቅሳቸው ነበር።
በፈረንጆቹ 1973 የተበረከተላቸው የኖቬል ሽልማትም አወዛጋቢ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ኪሲንጅር በካምቦዲያ የቦምብ ጥቃት እንዲፈጸም ሃሳብ አቅርበው በቬትናም ሰላም ለማስፈን ጥረት አድርገዋል በሚል ሽልማቱ መሰጠቱ ተገቢ አለመሆኑን ያነሱ ሁለት የኖቬል ሽልማት ኮሚቴ አባላትም ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸው አይዘነጋም።
ለአምስት አስርት አመታት የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የዘወሩት ሄነሪ ኪሲንጀር የሁለት ልጆች አባት ነበሩ።