የ2024 ዲቪ ሎተሪ እድለኞች ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ይፋ እንደምታደርግ አሜሪካ አስታወቀች
አሜሪካ ከዲቪ ሎተሪ ጋር በተያያዘ ከሀሰተኛ መረጃ እንዲጠነቀቁ አሳሰበች
የ2023 ዲቪ ሎተሪ አሸናፊ ኢትዮጵያዊያን በነበረው ጦርነት ምክንያት ተጎድተናል ማለታቸው ይታወሳል
አሜሪካ ከዲቪ ሎተሪ ጋር በተያያዘ ከሀሰተኛ መረጃ እንዲጠነቀቁ አሳሰበች።
አሜሪካ በዓለም ላይ በየዓመቱ 50 ሺህ ሰዎችን በዳይቨርሲቲ ቪዛ ወይም ዲቪ ሎተሪ አማካኝነት ወደ ሀገሯ ታስገባለች።
- የ2022 የአሜሪካ ዲቪ አሸናፊ ኢትዮጵያዊያን “ወደ አሜሪካ የመጓዝ እድላችን እየጠበበ ነው” አሉ
- አውሮፓ ከአሜሪካ ተጽዕኖ ልትላቀቅ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ማክሮን ተናገሩ
ባሳለፍነው ጥቅምት እና ህዳር ወራት ላይ በበይነ መረብ አማካኝነት የተሞላው የ2024 ዲቪ ሎተሪ አሸናፊዎች መታወቃቸው ተገልጿል።
የዲቪ 2024 ማመልከቻ የሞሉ ዜጎችም መመረጣቸውን እና አለመመረጣቸውን የፊታችን ቅዳሜ ማለትም ከሚያዚያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ማወቅ እንደሚችሉ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ በትዊተር ገጹ ጽፏል።
ኢምባሲው አክሎም በዲቪ ሎተሪ ድረገጽ ላይ በመግባት አመልካቾች ያመለከቱበትን ልዩ ቁጥር ወይም ኮድ በማስገባት ማወቅ ይችላሉም ብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለም የድቪ ሎተሪ አሸንፋችኋል፣ ከአሜሪካ ኢምባሲ ነው እምንደውለው በሚል የሚያጭበረብሩ አካላት ስለሚኖሩ አመልካቾች እንዲጠነቀቁ አሳስቧል።
ዲቪ ሎተሪ ስለማሸነፋቸው እና አለመድረሱን አመልካቾች በራሳቸው እጃቸው ላይ ባለው ሚስጢራዊ ቁጥር ማረጋገጥ ብቸኛው መንገድ እንደሆነም ተገልጿል።
የ2023 ዲቪ ሎተሪ አሸናፊዎች እስከ ቀጣዩ መስከረም 2016 ዓ.ም ድረስ ብቻ እንደሚስተናገዱም ኢምባሲው በመግለጫው ላይ ጠቁሟል።
የ2022 ዲቪ ሎተሪ አሸናፊዎች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መከሰቱን ተከትሎ የአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት በመሻከሩ ተጎድተናል ማለታቸው ይታወሳል።
ዲቪ ከደረሳቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል አስተያየታቸውን ለአልዐይን የሰጡ የድቪ 2022አሸናፊዎች በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከር ምክንያት እድሉን ተጠቅመን ወደ አሜሪካ እንዳንሄድ ተደርገናል ብለውም ነበር።
በኢትዮጵያ ያለው የአሜሪካ ኢምባሲ በበኩሉ " የዲቪ ሎተሪ እድለኛ ተሆነ ማለት ቪዛ ይገኛል፣ ለቪዛ ቃለ መጠይቅም ይጠራል ወይም ቪዛ ይሰጣል ማለት አይደለም" ሲል በወቅቱ ምላሽ ሰጥቷል።
ነገር ግን የዲቪ ሎተሪ እድለኛ መሆን የቪዛ ጥያቄ ለማቅረብ የመጀመሪያው መስፈርት ነው ያለው ኢምባሲው እድለኞቹ አሁን ላይ የቪዛ አገልግሎት ሂደት ውስጥ ሳይገቡ ከቀረ በቀጣይ በሚደረጉ ተመሳሳይ የቪዛ አገልግሎት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ ሲልም አክሎ ነበር።
አሜሪካ በየዓመቱ ከአፍሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ እና አውስትራሊያ 50 ሺህ ሰዎችን በድቪ ሎተሪ ወደ ሀገሯ ታስገባለች።
አፍሪካ የዚህ እድል ትልቁን ኮታ የምትሸፍን ሲሆን በዲቪ 2022 ፕሮግራም ግብጽ፣ አልጀሪያ እና ሱዳን እያንዳንዳቸው 6 ሺህ ሰዎች እድለኞች ሲሆኑ ሞሮኮ 4 ሺህ 138 ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ 3 ሺህ 347 ፣ጋና 3 ሺህ 145 ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ 2 ሺህ 988 ሰዎች የዲቪ እድለኛ እንደሆኑ ከተቋሙ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።