የድቪ 2025 አሸናፊዎች ይፋ ሆኑ
የድቪ 2024 እድለኞች የቪዛ ማመልከቻ የፊታችን መስከረም ወር ያበቃል
የድቪ 2025 አሸናፊዎች እስከ ቀጣዩ መስከረም ወር ድረስ የሚስጢር ቁጥራቸውን መያዝ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል
የድቪ 2025 አሸናፊዎች ይፋ ሆኑ፡፡
ካሳለፍነው ጥቅምት እስከ ህዳር ወር ድረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት የተሞላው የድቪ 2025 አሸናፊዎች ታውቀዋል፡፡
የድቪ 2025 አመልካቾች ከዛሬ ጀምሮ ለዚህ እድል መመረጣቸውን እና አለመመረጣቸውን በእጃቸው ላይ ባለው የማመልከቻ ኮድ ተጠቅመው ማወቅ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
የድቪ 2025 አመልካቾች በ https://dvprogram.state.gov/ESC/ ድረገጽ ላይ በመግባት ማረጋገጥ ይችላሉ የተባለ ሲሆን የሚስጢር ቁጥራቸው የጠፋባቸው አመልካቾች ደግሞ በ https://dvprogram.state.gov/ESC/CheckConfirmation.aspx በመግባት ደግመው ማግኘት ይችላሉም ተብሏል፡፡
የድቪ 2025 አሸናፊዎች መሆናቸውን ያረጋገጡ አመልካቾች የሚስጥር ቁጥራቸውን እስከ ቀጣዩ መስከረም 2017 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ድረስ መያዝ እንዳለባቸውም የሀገሪቱ ስቴት ዲፓርትመንት አስታውቋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት የተሞላው ድቪ 2024 አመልካቾች ወደ አሜሪካ ለመጓዝ የቪዛ ጥያቄዎችን የሚያቀርቡበት ጊዜ የፊታችን መስከረም 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃልም ተብሏል፡፡
እንደ መረጃው ከሆነ ከጥቅምት 2017 ዓ.ም በኋላ የቪዛ ጥያቄ ማቅረብ የሚችሉት የድቪ የ2025 አሸናፊዎች ብቻ ይሆናሉ፡፡
የ2022 ዲቪ ሎተሪ አሸናፊዎች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መከሰቱን ተከትሎ የአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት በመሻከሩ ተጎድተናል ማለታቸው ይታወሳል።
ዲቪ ከደረሳቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል አስተያየታቸውን ለአልዐይን የሰጡ የድቪ 2022 አሸናፊዎች በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከር ምክንያት እድሉን ተጠቅመን ወደ አሜሪካ እንዳንሄድ ተደርገናል ብለውም ነበር።
ድቪ ሎተሪ ሲሞላ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ስህተቶች ምን ምን ናቸው?
በኢትዮጵያ ያለው የአሜሪካ ኢምባሲ በበኩሉ " የዲቪ ሎተሪ እድለኛ ተሆነ ማለት ቪዛ ይገኛል፣ ለቪዛ ቃለ መጠይቅም ይጠራል ወይም ቪዛ ይሰጣል ማለት አይደለም" ሲል በወቅቱ ምላሽ ሰጥቷል።
አሜሪካ በየዓመቱ ከአፍሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ እና አውስትራሊያ 50 ሺህ ሰዎችን በድቪ ሎተሪ ወደ ሀገሯ ታስገባለች።
አፍሪካ የዚህ እድል ትልቁን ኮታ የምትሸፍን ሲሆን በዲቪ 2022 ፕሮግራም ግብጽ፣ አልጀሪያ እና ሱዳን እያንዳንዳቸው 6 ሺህ ሰዎች እድለኞች ሲሆኑ ሞሮኮ 4 ሺህ 138 ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ 3 ሺህ 347 ፣ጋና 3 ሺህ 145 ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ 2 ሺህ 988 ሰዎች የዲቪ እድለኛ እንደሆኑ ከተቋሙ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።