ፕሬዘዳንቱ ወደ ቴህራን ተጉዘው ከኢራኑ አቻቸው ጋር በሁለትዮሽ ንግድ ዙሪያ እመክራለሁ ብለዋል
የቬንዙዌላው ፕሬዘዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ኢራንን ሊጎበኙ መሆኑን አስታወቁ፡፡
የደብብ አሜሪካዋ ሀገር ቬንዙዌላ ፕሬዘዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ኢራንን እንደሚጎበኙ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዘዳንቱ ወደ መካከለኛዋ ምስራቅ ኢራን የሚያቀኑት በነዳጅ ሀብት አጠቃቀም እና ተያያዥ ቴክኖሎጂ ልማት ዙሪያ ለመምከር መሆኑን ጽህፈት ቤታቸው በድረገጹ አስነብቧል፡፡
ኢራን እና ቬንዙዌላ ከአሜሪካ ጋር በገቡበት ውዝግብ ምክንያት ምርቶቻቸውን ወደ ዓለም ገበያ አውጥተው እንዳይገበያዩ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በነዳጅ ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት የተትረፈረፈ ምርቶች ቢኖራቸውም በአሜሪካ በተጣለባቸው ማዕቀብ ምክንያትም እንደፈለጉ የንግድ ስራቸውን ማካሄድ አልቻሉም፡፡
ኢራን ለቬንዙዌላ የነዳጅ ቴክኖሎጂ ማሽኖችን በመርዳት ላይ ስትሆን ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናትን ደግሞ ከካራካስ ወደ ቴህራን እንደምታጓጉዝ ተገልጿል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በማደግ ላይ ሲሆን የፕሬዘዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ኢራንን መጎብኘት አዳዲስ የንግድ እና ወታደራዊ ደህንነት ስምምነቶችን በመፈረም ትብብራቸውን እንደሚያሳድገው ይጠበቃል፡፡
ማዱሮ ስል ቴህራን ጉብኝታቸው እንዳሉት "ወደ ቴህራን በቅርቡ እጓዛለሁ፣ ከኢራኑ ፕሬዘዳንት ኢብራሂም ሬይሲ ጋር እወያያለሁ ፣የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን የሚያሻሽሉ አዳዲስ ስምምነቶችንም እንፈራረማለን" ብለዋል፡፡
ይሁንና ፕሬዘዳንት ማዱሮ መቼ ወደ ቴህራን እንደሚጓዙ ባይናገሩም አገራቸው በፈረንጆቹ 2022 ዓመት ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር በቅርበት እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡
ቬንዙዌላ በድፍድፍ ነዳጅ የታደለች ሀገር ብትሆንም አሜሪካ በ2019 ዓመት በጣለችባት ማዕቀብ ምክንያት ሀብቷን ሸጣ መጠቀም አለመቻሏ ቬንዙዌላዊያንን ለስደት እና ለእንግልት ዳርጓል፡፡