የአሜሪካ ትምህርት ዲፓርትመንት ግማሽ ገደማ ሰራተኞቹን ሊቀንስ ነው
ዲፓርትመንቱ እንደገለጸው ፕሬዝደንት ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን በሚፈጽሙት ወቅት የዲፓርትመንቱ ሰራተኞች 4133 ነበሩ

ፕሬዝደንት ትራምፕና ቢሊየነሩ ኢለን መስክ የአሜሪካ የፌደራል መንግስት ግዙፍና አባካኝ ነው በሚል መጠነሰፊ የሰው ኃይል ቅነሳ ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል
የአሜሪካ ትምህርት ዲፓርትመንት (ሚኒስቴር) የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን እቅድ ለማሳካት ግማሽ ገደማ ሰራተኞቹን እንደሚቀንስ በትናንትናው እለት አስታውቋል።
ዲፓርትመንቱ ባወጣው መግለጫ እንዲባረሩ የተለዩ ሰራተኞች ከሳምንት በኋላ አስተዳደራዊ እረፍ ይሰጣቸዋል ብሏል።
ከጥቂት ቀናት በፊት እጩነታቸው በኮንግረሱ የጸደቀላቸው የትምህርት ጸኃፊዋ ሊንዳ ማክማሆም "የሰራተኛ ቅነሳው የትምህርት ዲፓርትመንቱ ለውጤታማነት፣ ለተጠያቂነትና ሀብት ለዋነኛ ተጠቃሚዎች በቀጥታ ለማድረስ ያለውን ቁርጠኛነት የሚያንጸባርቅ ነው። ታታሪ ሰራተኞቻችን ለዲፓርትመንቱ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አደንቃለሁ። ይህ የአሜሪካን ታላቅነት ለመመለስ ወሳኝ እርምጃ ነው" ብለዋል።
ዲፓርቱመንቱ እንገደጸው ለተማሪዎች የሚደረግን ብድር፣ የፋይናንስ ስጦታና ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚደረጉ እርዳታዎችን ጨምሮ ከዚህ በፊት የነበሩ መርሃግብሮችን ይቀጥላል። ተማሪዎችን፣ የተማሪ ቤተሰቦችን፣ አስተማሪዎችንና ግብር ከፋዮችን የበለጠ ለማገልገል በዲፓርትመንቱ ስር ያሉ ሁሉም ክፍሎች የቅነሳ ሰለባ እንደሚሆኑ ጠቅሷል።
ዲፓርትመንቱ እንደገለጸው ፕሬዝደንት ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን በሚፈጽሙት ወቅት የዲፓርትመንቱ ሰራተኞች 4133 ነበሩ። ቅነሳው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ዲፓርትመንቱ የሚኖሩት ሰራተኞች ቁጥር 2183 ይሆናል።
ይህ ቅነሳ በፈቃዳቸው የለቀቁትን 600 ሰራተኞችና ባለፉት ሰባት ሳምንታት የጡረት እድል ያገኙትን የሚያካትት ነው።
ፕሬዝደንት ትራምፕና የመንግስት አሰራር ውጤታማነት ዲፓርትመንት(ዶጅ) ኃላፊ አድርገው የሾሙት ቢሊነሩ ኢለን መስክ የአሜሪካ የፌደራል መንግስት ግዙፍና አባካኝ ነው በሚል መጠነሰፊ የሰው ኃይል ቅነሳ ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል።
ዶጅ እያካሄደ ባለው የሰራተኛ ቅነሳ እስካሁን 105 ቢሊዮን ዶላር መቆጣብ መቻሉን ገልጿል፤ ነገርግን ለህዝብ ይፋ ያደረገው እጅግ ጥቂቱን ነው።
ዶጅ በአሜሪካ ፌደራል መንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ከተቀጠሩ 2.3 ሚሊዮን ሰራተኞች ውስጥ ከ100ሺ በላይ ሰራተኞች ቀንሷል ተብሏል።