የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግለት ጠየቀ
ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ወታደራዊ አዛዦች የአንድ ጠባብ ቡድንን የስልጣን ጥም ለማርካት የመፈንቅለ መንግስት እንስቃሴ እያደረጉ ነው” ብሏል

አቶ ጌታቸው “ህገ ወጥ እንቅስቀሴን ለመቃወም በወጡ ዜጎች ላይ በተከፈተ ተኩስ በአዲጉዱምና በመቀሌ ጉዳት ደርሷል” ብለዋል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግለት በይፋ ጠየቀ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ነው የፌደራል መንግስትን እገዛ የጠየቀው።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው “ከጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ አንዳንድ የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች ከተልኮ ወጭ የአንድ ጠባብ ቡድን የስልጣን ጥም ለማርካት በማለት ግልፅ የመፈንቅለ መንግስት እንስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል” ብሏል።
“በዚህ ሳምንትም በተመሳሳይ በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ግንባር አዛዦች እንቅስቃሴው በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል” ብሏል መግለጫው።
ይህንን አደገኛ እንቅስቃሴ ለመግታት እና ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ሁሉ ለማስቆም የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ለትግራይ ጦር ዋና አዛዥ ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ትእዛዝ ቢሰጥም ማስቆም እንዳልቻለ አስታውቋል።
ሁኔታው እልባት ባለማግኘቱ የግንባሩ የጦር አዛዦች እገዳ እንደተጣለባቸው ያመላከተው መግለጫው፤ የጸጥታ ቢሮ እንዲመራ የተሾመው አካል ህግ ከመጠበቅ ይልቅ ከወንጀለኞች ጎን በመቆም መግለጫ አውጥቷል ብሏል።
ይህንን ተከትሎም የጸጥታው ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ ከኃላፊነታቸው እንደተነሱም መግለጫው አመላክቷል።
በአሁኑ ሰዓት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እየተፈፀመ መሆኑን ያስታወቀው ጊዜያዊ አስተዳሩ፤ “የመንግስ መዋቀቅርን ከላይ እስከታች የማፍረስ እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል” ብሏል።
“የትግራይ ጦር ከፍተኛ አዛዦች የኃላ ቀሩን ቡዱን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ መንግስት እንዲፈርስ እንዲሁም የፕሪቶርያ ስምምነት በይፋ እንዲጣስ በማድረግ የትግራይን ህዝብ ዳግም ወደ ሌላ የጥፋት ጦርት እያስገቡ ነው” ብሏል መግለጫው።
አስተዳሩ አክሎም “የፌደራል መንግስት በጸጥታ ሃይሎች ስም የሚንቀሳቀሱት ኋላ ቀር እና ወንጀለኛ ቡድን ተላላኪዎች መሆናቸውንና የትግራይን ህዝብና ጊዜያዊ አስተዳደር የማይወክሉ መሆናቸውን ተረድቶ አስፈላጊውን እርዳታ ሊያደርገወ ይገባል” ሲልም ጠይቋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት ምሽት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰራጩት ጽሁፍ ህገ ወጥ እንቅስቀሴን ለመቃወም በወጡ ዜጎች ላይ በተከፈተ ተኩስ በአዲጉዱምና በመቀሌ ጉዳት መደረሱን አስታውቀዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ “ጥቂት የሰራዊት አዛዦች ቡድን የመንግስት መዋቅሮች እንዲፈርሱ ባሳለፈው የተሳሳተ ውሳኔ ክልሉን ወደ ከፍተኛ ችግር ከቶታል” ብለዋል።
“ይህንን ህገ ወጥ እንቅስቀሴ ለመቃወም በአደባባይ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይም ይህ ህገ ወጥ ቡድን ተኩስ ከፍቶ በአዲ ጉዶም እና በመቀሌ የተወሰኑ ክፍሎች በሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል” ሲሉም ገልጸዋል።
ቡድኑ እያደረገ ያለው እንቅቃሴ “ወረራ” ነው ያሉት አቶ ጌታቸው እቅስቀሴውም ህገ ወጡን የህወሓት ቡድን ወደ ስልጣን ለማምጣት እንደሆነም አስታውቀዋል።
የትግራይ ህዝብ ወደ አውዳሚ ጦርነት ከማምራቱ በፊት የፕሪቶሪያ ስምምነት ባለድርሻ አካላት ሁሉ ይህን የመሰለ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ሊያስቆሙ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ በሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳር እና በዶ/ር ደብረጺዮን መካከል ካሳለፍነው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የተፈጠረው አለመግባባት እየተባባሰ ይገኛል።
አለመግባባቱ ካሳለፍነው ሰኞ ምሽት ጀምሮ ወደ መካከር የተሸጋገረ ሲሆን፤ በአንድ አንድ የክልሉ አካባዎች ላይም ግጭቶች ተስተውለዋል።
አለመግባባቱ እንደ አዲስ የተካረረው ባሳለፍነው ሰኞ ምሽት በአቶ ጌታው ረዳ የተጻፈ ደብዳቤ ሶስት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ማለትም፤ ሜጀር ጀነራል ዮሃንስ ወልደጊዮርጊሰ፣ ሜጀር ጀነራል ማሾ በየነ እና ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ሀይለ በግዜያዊነት መታገዳቸውን ተከትሎ ነው።
የእግድ ደብዳቤውን ተከትሎ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ትናንት ጠዋት ባወጣው መግለጫ “የእግድ ውሳኔው በግል የተወሰደና ያልሾመውን ያወረደ ነው” እንዲሁም “ተቋማዊ አሰራርንና ህግን ያልተከተለ ነው” በማለት ውድቅ ማድረጉ ይታወቃል።
በደብረጺን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓትም በሶስት የትግራይ ሰራዊት አዛዦች ላይ የተላለፈውን እግድ “የማይተገበር ነው” ሲል ውድቅ አድርጎታል።
በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት ሌሊት በማበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫው፤ አቶ ጌታቸው ረዳን ከስልጣን ማንሳቱን በማስታወስ፤ እገዳውን “እጃቸው ላይ በሌለ ስልጣን የወሰዱት እርምጃ ነው” በማለት አጣጥሎታል።