ዩክሬን ኢራን ለሩሲያ የባለስቲክ ሚሳይል አስታጥቃለች የሚለው ሪፖርት እረፍት ነስቶኛል አለች
የዩክሬን ዋነኛ አጋር የሆነችው አሜሪካም ኢራን ሚሳይል ለሩሲያ አሳልፋ ልትሰጥ ትችላለች የሚል ስጋቷን ገልጻለች
ዩክሬን በቴህራን እና በምስኮ መካከል ያለው ጥልቅ ግንኙነት ለዩክሬን፣ የአውሮፓ እና ለመካከለኛው ምስራቅ ስጋት ነው ብሏል
ዩክሬን ኢራን ለሩሲያ የባለስቲክ ሚሳይል አስታጥቃለች የሚለው ሪፖርት እረፍት ነስቶኛል አለች።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢራን የባለስቲክ ሚሳይሎች ተላልፈው ወደ ሩሲያ እጅ ሊገቡ ነው የሚለው ሪፖርት እረፍት እንደነሳው በትናንትናው እለት አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ለጋዜጠኞች በላከው የኢሜል መልእክት በቴህራን እና በምስኮ መካከል ያለው ጥልቅ ግንኙነት ለዩክሬን፣ የአውሮፓ እና ለመካከለኛው ምስራቅ ስጋት መሆኑን ገልጾ፣ አለምአቀፉ ማህበረሰብ በኢራን እና በሞስኮ ላይ ጫና እንዲያሳድር ጥሪ አቅርቧል።
የአሜሪካው ሲኤንኤን ቴሌቪዥን እና ዎልስትሪት ጆርናል ኢራን የአጭር ርቀት ሚሳይል ለሩሲያ አስተላልፉ ሰጥታለች የሚል ሪፖርት ማውጣታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ ፋዝ-360 የተባለውን የኢራን የአጭር ርቀት ሚሳይል ለመቀበል እየጠበቀች መሆኑን እና ሩሲያም የሚሳይሉን አጠቃቀም እንዲያውቁ በደርዘን የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ለስልጠና ወደ ኢራን መላኳን ሮይተርስ ባለፈው ነሐሴ ወር ዘግቦ ነበር።
ባለፈው አርብ የዩክሬን ዋነኛ አጋር የሆነችው አሜሪካም ኢራን ሚሳይል ለሩሲያ አሳልፋ ልትሰጥ ትችላለች የሚል ስጋቷን ገልጻለች።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ሲአን ሴቭዋት ማንኛውንም የኢራንን ሚሳይል ለሩሲያ አስተላልፎ የመስጠት ሂደት ኢራን በዩክሬን ላይ ወረራ እያካሄደች ላለችው ሩሲያ የምትሰጠውን ድጋፍ ከፍ የሚያደግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተመድ የኢራን ልኡክ በዩክሬን ጉዳይ የኢራን አቋም አልተቀረም ብሏል።
"ኢራን ለጦርነቱ ተሳታፊዎች የጦር መሳሪያ ማቅረብ የሰዎችን ሞት እና የመሰረተልማቶችን ወድመት እንዲጨምር እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዳይደረስ ያደርጋል ብላ ታስባለች " ብሏል ልኡኩ።
ምዕራባውያን ሀገራት ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ በድብቅ የጦር መሳሪያ እያቀረቡ ነው የሚል ክስ ያቀርባሉ።ሰሜን ኮሪያ እና ኢራን ይህን ክስ አይቀበሉትም።