ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ግብፅ፣ ዩኤኢ እና ቱርክ ሊጓዙ መሆኑን ገለጹ
ኔድ ፕራይስ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ወታደራዊ መፍትሄ ሲሉ በተደጋጋሚ ገልጸዋል
ህወሓት በሴሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተጀመረው ግጭት አንድ አመት አልፎታል
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፣ ቱርክ እና ግብፅ ሊጓዙ መሆኑን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ፤ ፌልትማን ወደ ካይሮ፣ አቡዳቢና አንካራ የሚጓዙት በኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ዙሪያ ለመምከር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት የአፍሪካ ቀንድን ሰላምና ጸጥታ አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችልም አሜሪካ እምነቷ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኔድ ፕራይስ፤ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ያነሱ ሲሆን ትናንትናም ይህንን ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታው የሚታወስ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለው ችግር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት እያደረጉ ያሉ ዲፕሎማት መሆናቸውን ኔድ ፕራይስ ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት ጦርነት ውስጥ ከገቡ አንድ ዓመት ተቆጥሯል፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ህወሓት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ከተገለጸ በኋላ ይፋዊ ጦርነቱ አሁንም ቀጥሏል፡፡
ከሰሞኑም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሁሉም ግንባር ያለውን ጦር በመምራት ግንባር መሰንበታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡