አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በአይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለ አዲስ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተስመቷል
አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ስምምነት ሰው ሰራሽ ክህሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ላይ ያተኮረ ነው
ስምምነቱ የበለጠ ቀልጣፋ የአደጋ ጊዜ ምላሾችን፣ የኤሌክትሪክ አውታሮች አያያዝና ሌሎች ጥቅሞችን ያስገኛል ተብሏል
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በአይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለ የሰው-ሰራሽ ክህሎት ስምምነት አድርገዋል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ግብርናን፣ ጤና አጠባበቅን፣ ድንገተኛ ምላሽን፣ የአየር ሁኔታ ትንበያን እና የኤሌክትሪክ አውታርን ለማሻሻል ሰው-ሰራሽ ክህሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) አጠቃቀምን ለማፋጠንና ለማሻሻል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ስምምነቶች የግላዊነት መብትን ማሳደግ በመሳሰሉት ልዩ ቦታዎች ላይ ብቻ የተገደቡ መሆናቸውን ሮይተርስ ያናገራቸው የአሜሪካ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች መረጃዎቻቸውን ባለበት በመያዝ የጋራ የሰው-ሰራሽ ክህሎት ሞዴል ይገነባሉ ተብሏል።
ይህ ተነሳሽነት መንግስታት የበለጠ በመረጃ የበለጸጉ የሰው-ሰራሽ ክህሎት ሞዴሎችን ተደራሽ እንዲያደርጉ የሚያስችል እንደሆነ ተጠቅሷል።
ይህም የበለጠ ቀልጣፋ የአደጋ ጊዜ ምላሾችን፣ የኤሌክትሪክ አውታሮች አያያዝና ሌሎች ጥቅሞችን ያስገኛል ተብሏል።
በአዲሱ አጋርነት ሁሉም መረጃዎች ለድንገተኛ አደጋ አስተዳዳሪዎች፣ የኤሌክትሪክ አቅራቢዎችና ሌሎች ስርዓቶችን ለማሻሻል በሰው-ሰራሽ ክህሎት ላይ ለሚተማመኑ ሰዎች የተሻለ ውጤት የሚያስገኝ አንድ የጋራ ሞዴል" ጥቅም ላይ እንደሚውል ተነግሯል።
ትብብሩ በአሁኑ ጊዜ በዋይት ሀውስ እና በ 27ቱ የአውሮፓ ህብረት ስራ አስፈፃሚ በሆነው በአውሮፓ ኮሚሽን መካከል ነው።
የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለስልጣን በመጪዎቹ ወራት ሌሎች ሀገራት እንዲቀላቀሉ ይጋበዛሉ ብለዋል።