የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስራኤልንና የአረብ ሀገራትን የሚጎበኙት ፕሬዝደንት ትራምፕ ያቀረቡት ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማፈናቀል እቅድ ከፍተኛ ውግዘት ካስከተለ በኋላ ነው
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/07/243-123232-img-20250207-112907-936_700x400.jpg)
የፍልስጤም አስተዳደርና የአረብ ሀገራትን የትራምፕን ሀሳብ በጽኑ ተቃውመውታል
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ሩቢዮ እስራኤልንና የአረብ ሀገራትን የሚጎበኙት ፕሬዝደንት ትራምፕ ያቀረቡት ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማፈናቀል እቅድ ከፍተኛ ውግዘት ካስከተለ በኋላ ነው።
ሩቢዮ ከየካቲት 13-18 ባሉት ቀናት ወደ ሙኒክ የደህንነት ስብሰባ፣ እስራኤል፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ኳታር እና ሳኡዲ አረቢያ እንደሚጓዙ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ፍልስጤማውያን ከጋዛ እንዲፈናቀሉና አሜሪካ ቦታውን እንድትቆጣጠር ሀሳብ አቅርበዋል። ይህ የትራምፕ ሀሳብ ከመብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ውግዘት አጋጥሞታል።
ሩቢዩ ባለፈው ረቡዕ እለት ፍልስጤማውያን የሚፈናቀሉት ለ16 ወራት በዘለቀ ጦርነት የፈራረሰችው ጋዛ እስከምትጸዳና እስከምትገነባ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ሩቢዮ በጉብኝታቸው ስለጋዛ እና ሀማስ ጥቅምት 7፣ 2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ስላሉ ሁኔታዎች እንደሚወያዩ እንዲሁም ትራምፕ በቀጣናው እያራመዱ ያሉት አዲስ ፖሊሲ ቅቡል እንዲሆን እንደሚያግባቡ ገልጸዋል።
"ስታተስ ኮው(የቀደመው አሰራር) ሊቀጥል አይችልም። ፕሬዝደንት ትራምፕና ማርኮ ሩቢዮ ነገሮች መቀየር አለባቸው ብለው ያምናሉ" ብለዋል ባለስልጣኑ።
ከባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ ትራምፕ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን እንደ ግብጽና ጆርዳን በመሳሰሉት የቀጣናው አረብ ሀገራት መወሰድ እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን የፍልስጤም አስተዳደር ባለስልጣንና የአረብ ሀገራት ሀሳቡን በጽኑ ተቃውመውታል።
የትራምፕ አስተያየት የፍልስጤማውያን የቆየ የመፈናቀል ስጋት የሚያስተጋባ ነው።
የአሜሪካ አጋር የሆነችው እስራኤል 16 ወራት የዘለቀውን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ ኡቀም ስምምነት ከመደረሱ በፊት በፈጸመችው መጠነሰፊ ጥቃት ከ47 ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገዳላቸው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ለአስርት አመታት ባስቆጠረው የእስራኤል-ሀማስ ግጭት ውስጥ ከባድ ደም መፋሰስ ያስከተለው የቅርብ ጊዜው ግጭት የተቀሰቀሰው ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት አድርሶ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 250 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው።
በጋዛ ባካሄደችው ዘመቻ የዘር ማጥፋት ክስ የቀረበባት እስራኤል ክሱን አስተባለለች።