ለአለም ይበቃል የተባለው የአሜሪካ የሊቲየም ክምችት
በደቡብ ምስራቃዊ ኦሪገን የተገኘው የሊቲየም ክምችት 130 ሚሊየን ቶን እንደሚደርስ ተገልጿል
አሜሪካ ከፍተኛ የሊቲየም ሀብት ቢኖራትም በማምረት ረገድ ከአለም ያላት ድርሻ 1 በመቶ ብቻ ነው
አሜሪካ ከራሷ አልፎ ለአለም የሚበቃ የሊቲየም ክምችት ማግኘቷ ተነግሯል።
ቢዝነስ ኢንሳይደር እንደዘገበው በደቡብ ምስራቃዊ ኦሪገን እና ሰሜን ኔቫዳ “ማክደርሚት ካልዴራ” የተባለው አካባቢ 130 ሚሊየን ቶን የሊቲየም ሃብት እንዳለው ተረጋግጧል።
ከ16 ሚሊየን አመት በፊት በተከሰተ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተፈጠረው የማክደርሚት ሃይቅ የያዘው የሊቲየም ሃብት አሜሪካ ሊቲየም ከውጭ ሀገራት ማስገባት እንድታቆም ያደርጋታል ተብሏል።
የሊቲየም ክምችቱን ማውጣት ከተቻለ ለመላው አለም ለአስርት አመታት እንደሚበቃም ነው ዘገባው ያብራራው።
አሜሪካ በምድሯ 8 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የሚጠጋ የሊቲየም ክምችት አላት።
ይህም በሊቲየም ሃብታቸው ከፊት ከተቀመጡ አምስት ሀገራት አንዷ ያደርጋታል። ይሁን እንጂ በሊቲየም ምርት (ማውጣት) አሜሪካ ከአለም ሀገራት ያላት ድርሻ 1 በመቶ ብቻ ነው።
በዚህም አሜሪካ ለኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ብሎም ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወሳኝ ግብአት የሆነውን ሊቲየም ከሌሎች ሀገራት ታስገባለች።
በ2020 ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘውና በቅርቡ በምርምር ዳግም የተረጋገጠው ግዙፍ ክምችት ግን ዋሽንግተን ከራሷ አልፋ ለሌሎችም መትረፍ የሚያስችላት ነው ተብሏል።
የ“ማክደርሚት ካልዴራ” አካባቢ ነዋሪዎች ግን ስፍራውን “ቅዱስ ነው” በማለት የተፈጥሮ ሃብቱን የማውጣት ጥረቱን እየተቃወሙ ነው።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በብዛት የማምረት ፉክክሩ በቀጠለበት በዚህ ወቅት አሜሪካ ይህን ተቃውሞ የምትሰማ ግን አይመስልም።